የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የአቶ ሀይለማርያምን ሹመት እንደምትቀበለው አስታወቀች

መስከረም ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የክቡር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝን በጠቅላይ ሚኒስትርነት መመረጥና የክቡር አቶ ደመቀ መኮንን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን መመረጣቸውን በማስመልከት ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ፕ/ት ቤት ያስተላለፈችው መልክት” በሚል ርእስ ትናንት ባወጣችው መግለጫ ለአቶ መለስ ዜናዊ አመራር የነበራትን አድናቆትም ገልጣለች።

ቤተክርስቲያኑዋ ” ይህ ያለፈው ዘመን ለአገራችንና ለአፍሪካ ብሎም ለአለም ህዝብ ትልቅ ሚና የነበራቸውን ሁሉ ታላቅ መሪዎች ያጣንበት ዘመን በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዘንድ ትልቅ ሀዘን ሆኖ ሰንብቷል።” ብላለች።

ቤተክርስቲያኑዋ በመያያዝም ” የህዝባችንን የልማት አንድነት ያጠናከረውና የመንግስታችንን ፖሊሲ በቁርጠኝነት ለማስፈጸም ቀን ከሌሊት ውድ ጊዜያቸውን ለህዝብ ሲሉ እየሰሩ ያለፉት የህዳሴ ግድቡን በማስጀመር ” አባይን የደፈረ ጀግና” በሚል የተጠሩት የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ራእይን እውን እንዲሆን ቤተክርስቲያናችን ተከታይ ምእመናንና አገልጋይ ካህናቱን በሜአዝ የጀመረችውን የማሳካት እንቅስቃሴ አሁንም ህዝቧንና ያላትን አቅም በመጠቀም ለተግባራዊነቱ ከመንግስት ጎን እንደ ምትንቀሳቀስና መንግስት ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለመደገፍ ቅድመ ዝግጅቷን አጠናቃለች” በማለት ገልጣለች።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ዛሬም እንደጥንቱ ከመንግስት ጋር በቁርጠኝነት ለመስራት ዝግጁ ናት በማለት አቋማን ገልጣለች።

በሌላ ዜና ደግሞ አልጀዚራ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ያልሆኑ ጠቅላይ ሚኒሰትርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተሾሙ በማለት ዘግቧል።

ሁለቱም ተሻሚዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አባላት አለመሆናቸውን የታዘቡ አንድ የምእራብ ዲፕሎማት ” በአሁኑ ሰአት የፕሮቴስታንት ተከታይ የሆነ ወላይታ እና ሙስሊም የሆነ አማራ በከፍተኛ የስልጣን ቦታዎች ላይ ማየት ያስገርማል” ብለዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide