በቂ የውጪ ምንዛሬ ያለው በወጋገን ባንክ ብቻ ነው ተባለ

መስከረም ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የአገሪቱ ባንኮች በውጪ ምንዛሬ እጥረት በተጠቁበት በአሁኑ ጊዜ የወጋገን ባንክ ደንበኞች ብቻ ያለምንም እጥረት ንግዳቸውን እያቀላጠፉ መሆናቸው ተጠቆመ።

የአይ.ኤም.ኤፍ የ ኢትዮጵያ ተወካይ  አገሪቱ ለሁለት ወራት የሚበቃ የውጪ ምንዛሬ እንዳላት በቅርቡ ቢገልጹም ዋናውን ንግድ ባንክ ጨምሮ በ አገሪቱ የሚገኙ ባንኮች በሙሉ በከፍተኛ እጥረት በመጠቃታቸው ደንበኞቻቸውን ማገልገል እንደተሳናቸው  የአዲስ አበባ የ ኢሳት ወኪሎች ከተለያዩ ባንኮች ያሰባሰቧቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።

እቃ ከውጪ ለማስመጣት የሚፈልጉ ነጋዴዎች ወደ ባንኮች በመሄድ የውጪ ምንዛሬ ሲጠይቁ እስከ ስድስት ወራት ድረስ ወረፋ ጠብቁ እንደሚባሉ ለዘጋቢዎቻችን ገልጸዋል።

በዚህም ሳቢያ የንግድ እንቅስቃሴያቸው ክፉኛ በመዳከሙ ሥራቸውን ለማቆም የደረሱበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን እነዚሁ በአስመጪና ላኪነት ሥራ የተሰማሩ ነጋዴዎች ተናግረዋል።

“በጣም የሚያሳዝነው አብዛኛው ነጋዴ በውጪ ምንዛሬ እጥረት እጁን አጣጥፎ በተቀመጠበት በአሁኑ ጊዜ  የወጋገን ባንክ፤ የህወሀት አባላት ለሆኑ  ነጋዴዎች “ደንበኞቼ ናቸው” በማለት  እንደልብ ምንዛሬ እያቀረበላቸው ይገኛል” ያሉት ነጋዴዎቹ፤ የዋናው ንግድ ባንክ ደንበኞች ከ 4 እስከ 6 ወራት ጠብቁ እየተባልን፤  የወጋገኖቹ ግን ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሁለት ጊዜ እየተመላለሱ የውጪ ንግዱን ያጧጡፉታል” ብለዋል።

ወኪሎቻችን እንዳሉት፤እጅግ በርካታ አስመጪ ነጋዴዎች ፦”የዶላር ያለህ!” በማለት ሲያማርሩ መሰማት የየዕለቱ የተለመደ ትዕይንት ሆኗል። ወጋገን ባንክ በኢፈርት ስር ከሚገኙት የህወሀት ተቋማት አንዱ መሆኑ ይታወቃል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide