መጋቢት ፳፯ (ሀያ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በነገው ዕለት በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ የሚካሄደው የመለስ ፋውንዴሽን መስራች ጉባዔ ላይ 13 አባላት ያሉት
የቦርድ አባላት እንደሚመረጡና ፋውንዴሽኑ የመለስ ሁለት ልቦለድ መጽሐፍትን ጨምሮ ሌሎችንም ፖለቲካዊ ጹሑፎች
እንደሚያሳትም ተጠቆመ፡፡
አቶ መለስ ዜናዊ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በሞት ከተለዩ ከሰባት ወራት በላይ የተቆጠረ ሲሆን
ተተኪው አመራር የእሳቸውን ሌጋሲ ሳይበረዝ ሳይከለስ ለማስቀጠል በገባው ቃል መሰረት የመለስ ፋውንዴሽን
በመንግስት ደረጃ በአዋጅ በጥር ወር 2005 ዓ.ም እንዲቋቋም መደረጉ ይታወሳል፡፡
ፋውንዴሽኑ ቅዳሜ መጋቢት 28 ቀን 2005 ዓ.ም የመጀመሪያውን መስራች ጉባዔ የሚያካሂድ ሲሆን በዚህ ጉባዔ ላይ 13 አባላት ያሉትና ለመጪዎቹ አራት ዓመታት የሚያገለግሉ የቦርድ አባላትን ይመርጣል፡፡ ከነዚህ የቦርድ አባላት መካከል አራት ያህሉ ሰዎች ከአቶ
መለስ ቤተሰቦች የሚወከሉ ሲሆን በየአራት ዓመቱ የሚካሄደው የቦርድ አባላት ምርጫ ቤተሰቡን የሚመለከት
እንደማይሆን የፋውንዴሽኑ መመስረቻ አዋጅ ቁጥር 781/2005 ይጠቁማል፡፡
ፋውንዴሽኑ ከተመሰረተ በኃላ ከሚሰራቸው ተግባራት መካከል አቶ መለስ በትግል ወቅት በትግርኛ ቋንቋ የጻፉዋቸው
ሁለት ልቦለድ መጽሐፍት እንዲታተሙ ይደረጋል፡፡በተጨማሪም በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ያዘጋጁዋቸው
የተለያዩ የርዕዮተዓለም ድርሳናት እንዲሁ ታትመው የሚሰራጩ ሲሆን ገቢውም ለፋውንዴሽኑ ስራ እንደሚውል ታውቋል፡፡
በተጨማሪም ፋውንዴሽኑ የአቶ መለስ አስከሬን በቋሚነት የሚያርፍበት መናፈሻ መገንባትና ማስተዳደር፣ቤተመጽሐፍት
ማቋቋም፣ለደሃ ሴቶች የስኮላርሺፕ ዕድል መስጠትና የመሳሰሉ ተግባራት ይኖሩታል ተብሏል፡፡
የመለስ ፋውንዴሽን አብዛኛው የስራ ማስኪያጂያ ገንዘብ ከመንግስት ወጪ የሚሆን ነው። አንድ አስተያየት ሰጪ ሲናገሩ መለስን የማይደግፉ ግብር ከፋዮች ሳይወዱ በግድ ገንዘባቸው ለፋውንዴሽኑ እንዲሰጥ መደረጉ ተገቢ አይደለም ብለዋል። ግብር ከፋዮች ገንዘባቸው ለፋውንዴሽኑ ቢውል ተቃወማላችሁ ወይስ አትቃወሙም ተብለው ሊጠየቁ የገባ እንደነበር እኝህ አስተያየት ሰጪ ጠቁመው ፣ ያ ካልሆነ ግን ዜጎች በከፈሉት ግብር የሚተዳደረው መንግስት፣ ያለዜጎች ፈቃድ ገንዘባቸውን ለፋውንዴሽኑ እንዲሰጥ ማድረጉ አግባብ አይደለም ብለዋል።