የአቶ መለስ ዜናዊ መታሰቢያ ሀውልት ፈረሰ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 8/2010)

በአጋሮ ከተማ መሀል አደባባይ የቆመው የአቶ መለስ ዜናዊ መታሰቢያ ሀውልት ፈረሰ።

ፋይል

የከተማዋ ቄሮ በወሰደው ርምጃ ሀውልቱ ከቆመበት እንዲወገድ መደረጉ ታውቋል።

በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ህዝባዊ ተቃውሞው ቀጥሏል።

በአርሲ ኢተያ በሙስሊሙና ክርስቲያኑ መካከል የሃይማኖት ግጭት ለመቀስቀስ ሙከራ እየተደረገ ነው።

በጅማ አመጽ የተቀላቀለበት ተቃውሞ በመካሄድ ላይ ነው።

በሸዋ ሮቢት የአጋዚ ወታደሮች ግድያ መፈጸማቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

መሃል አጋሮ ከተማ የተተከለውና ለአቶ መለስ ዜናዊ መታሰቢያ የቆመው ሀውልት በቄሮዎች ርምጃ ተወስዶበታል።

ከዚህ ቀደም ሀውልቱ ላይ ቀለም በመድፋት ገጽታውን እንዲበላሽ ያደረጉት የአጋሮ ወጣቶች ዛሬ ሀውልቱን ሙሉ በሙሉ በማፈርስ አስወግደውታል።

የአቶ መለስ ዜናዊ ሀውልት በከተማችን መቆም አልነበረበትም ያሉት የአጋሮ ወጣቶች፣ ከነመጥፎ ታሪኩ ነቅለን አሰውግደናል ማለታቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በአርሲ ኢተያ በሙስሊምና ክርስቲያን እምነት ተከታዮች መካከል ግጭት ለመቀስቀስ እየተደረገ ያለውን ሴራ ህዝቡ እንዲያከሽፈው ተጠይቋል።

በኢተያ ውጥረት መንገሱን የጠቀሱት ምንጮች እስካሁን ሁለት ሰዎች መገደላቸውን ገልጸዋል።

እንዲህ ዓይነት ግጭት የሚቀሰቀሰው በአገዛዙ ካድሬዎች አማካኝነት እንደሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ከእርስ በእርስ ግጭት ህዝብ የሚያተርፈው ነገር ባለመኖሩ ራሱን እንዲጠብቅ የሀገር ሽማግሌዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ህዝባዊ ተቃውሞ ሲደረግ መዋሉ ታውቋል።

በሻሸመኔ፣ በሞጆ፣ በባሌ ሮቤና በጅማ ህዝቡ አደባባይ በመውጣት የህወሃትን አገዛዝ አውግዟል።

ከስልጣን እንዲወርድም ጠይቋል። በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለው ሁኔታም መረጋጋት እንዳላሳየ ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ዛሬ በለገጣፎና ሰበታ ሱቆችና መደብሮች እንደተዘጉ የዋሉ ሲሆን የአጋዚ ወታደሮች በብዛት ገብተው ነዋሪውን እያዋከቡት እንደነበር ተገልጿል።

በሃሮማያም ህዝባዊ ተቃውሞ መደረጉ ታውቋል።

በጅማ ሰሞንኑ የተደረገው ህዝባዊ አመጽ ዛሬም መቀጠሉን ለማወቅ ተችሏል።

በከተማዋ የተለያዩ መንደሮች መንገዶቻቸው በተቃጠሉ ጎማዎች ተዘግተዋል።

ሁኔታውን ለመቆጣጠር የአገዛዙ ታጣቂዎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውጤታማ አለመሆኑም ተመልክቷል።

በሌላ በኩል በሸዋ ሮቢት ከተማ በአጋዚ ወታደሮች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል።

በከተማዋ በመካሄድ ላይ ያለውን ህዝባዊ አመጽ ተከትሎ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ባልታወቁ ሃይሎች 3 የአጋዚ ወታደሮች መገደላቸውን መረጃዎች ያመልክታሉ።