የስራ ማቆም አድማው ወደ አደባባይ ተቃውሞ ተቀየረ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 8/2010)

በጉራጌ ዞን ወልቂጤ የስራ ማቆም አድማው ወደ አደባባይ ተቃውሞ ተቀየረ።

የተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ጥቃት ደርሶባቸዋል።

የግብር መሰብሰቢያ መስሪያ ቤት ህንጻ በእሳት ተቃጥሎ፣ ሰነዶች መውደማቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ቢያንስ የአንድ ሰው ህይወት መጥፋቱ እየተነገረ ነው።

ከጦላይ የጦር ማሰልጠኛ ካምፕ የመከላከያ ሰራዊት ወልቂጤ መግባቱንም ለማወቅ ተችሏል።

በከተማዋ ህዝባዊ አመጹ ተጠናክሮ መቀጠሉን ዘግይተው የሚወጡ መረጃዎችም አመልክተዋል።

የተጠራቀመ ብሶት አደባባይ ወጥቷል። የታመቀው በደል ፈንድቷል።

ለዘመናት የቆየው ፍርሃት ተሰብሯል ወልቂጤ ላይ።

ከሶስት ሳምንት በላይ ከመንግስት ምላሽ ሲጠብቅ የነበረው የወልቂጤ ነዋሪ በመጨረሻም ርምጃ ወሰዷል።

ለትላንት ቀጠሮ የተያዘለትን የስራ ማቆም አድማ ቃላቸውን በመጠበቅ ተግባራዊ ያደረጉት የወልቂጤ ነዋሪዎች በሁለተኛው ቀን ህዝባዊ አመጽ መጀመራቸውን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።

ትላንት ሱቆች ፣መደብሮችና ትምህርት ቤቶች በአጠቃላይ የወትሮው አንቅስቃሴ ቀጥ ብሎባት የዋለችው ወልቂጤ ዛሬ መንገዶቿ በተቃጠሉ ጎማዎች፣በድንጋይና በእንጨት ተዘግተዋል።

በመንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ ጥቃት ተሰንዝሯል።

በግብር የተማረረው ነዋሪ በከተማዋ የሚገኘውን የገቢዎች መስሪያ ቤት በማቃጠል ሰነዶቹን ማውደሙ ታውቋል።

ከተማዋ በጭስ ታፍና መዋሏን በፎቶግራፍና በምስል ተደግፎ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

የጉራጌ ዞን መስተዳደር ተሽከርካሪዎች በቃጠሎ መውደማቸው የተገለጸ ሲሆን የዞኑ አስተዳዳሪና የዞን ጉዳይ ሃላፊ መኖሪያ ቤቶች ላይም ጥቃት መሰንዘሩን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በእስካሁኑ ሂደት አንድ ሰው መገደሉ ተረጋግጧል። ሁለት ሰዎች መቁሰላቸውም ታውቋል።

የህዝቡ ቁጣና ርምጃ ተባብሶ መቀጠሉን ዘግይተው የሚወጡ መረጃዎች አመልክተዋል።

ዘግይቶ በደረሰን መረጃም ከጦላይ የጦር ማሰልጠኛ ካምፕ የመከላከያ ሰራዊት ወልቂጤ መግባቱ ታውቋል።

የህዝቡን ተቃውሞ ለማስቆም ከከተማዋ ፖሊስ አቅም በላይ መሆኑን ተከትሎ የገባው የመከላከያ ሰራዊት ተቃውሞውን ለመቆጣጠር የሃይል ርምጃ በመውሰድ ላይ እንደሆነም ተገልጿል።

ህዝቡ ግን ተቃውሞውን በማጠናከር በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ ርምጃ በመውሰድ ላይ ይገኛል።

ሆስፒታል ሊገነባለት ቃል የተገባለት የወልቂጤ ህዝብ የሆስፒታሉ በጀት ወደ ትግራይ ተዛውሯል የሚል መረጃ አፈትልኮ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በወልቂጤ የሕዝብ ተቃውሞ እየተጠናከረ መጥቷል።

ወደሌሎች አካባቢዎች ተቃውሞው ሊዛመት እንደሚችል እየተነገረ ነው።

ከአዲስ አበባ ጅማ የሚወስደው መንገድ ከወሊሶ በኋላ ተቋርጧል።

የትራንስፖርት አገልግሎትም ቆሟል።