የአቶ መለስ መንግሥት በ”ሽብርተኝነት‘ በወነጀላቸው ስምንት ተከሳሾች ላይ በዐቃቤ- ሕግ ተሸሻለ የተባለው የክስ ቻርጅ ዛሬ ቀረበ

ህዳር 20 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-የአቶ መለስ መንግሥት በ”ሽብርተኝነት‘ ከወነጀላቸው 24 የፖለቲካ ፓርቲ የአመራር አባላት፣ ጋዜጠኞች እና ነፃ አሳቢያን ኢትዮጵያዊያን ውስጥ ሀገር ውስጥ በእሥር ላይ በሚገኙት ስምንት ተከሳሾች ላይ
በዐቃቤ- ሕግ ተሸሻለ የተባለውን የክስ ቻርጅ ዛሬ አቀረበ፡፡ ይህ ተሸሻለ የተባለው የክስ ቻርጅ የቀድሞው አዲስ ነገር ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር እና ዋና አዘጋጅ የሆኑት ዐብይ ተክለማርያምና መስፍን ነጋሽን አያካትትም
ተብሏል፡፡

እነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ አንዳርጋቸው ጽጌ የተካተቱበት ከተከሳሽ ተራ ቁጥር 9 እስከ 24 ያሉት በውጭ አገራት የሚገኙት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በተደረገላቸው ጥሪ መሠረት ለህዳር 27 ቀን 2004 ዓ.ም ጊዜ ቀጠሮ እንደያዘላቸው ፍርድ ቤቱ ገልፆል፡፡

ዐቃቤ-ሕግ የፌዴራል ፖሊስ በእስር ላይ ባዋላቸው ከተከሳሽ ተራ ቁጥር 1 እስከ 8 ድረስ ያሉት ተከሳሾች ላይ አሻሻልኩ ያለውን ክሥ 1 እና ክስ 4  ከሌሎች ክሶች ጋር አንድ ላይ በ14 ገጽ ያቀረበ ሲሆን፣ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ክሱን ለተከሳሾች በንባብ አሰምቷል፡፡

የተከሳሽ ጠበቆች አቶ ደርበው ተመስገን እና አቶ ሣሙኤል አባተ በተሻሻለው አራተኛው ክስ (አሸባሪን በመተባበር) ላይ ተቃውሞ እንደሌላቸው የገለጹ ሲሆን በአንደኛው (ከአሸባሪዎች ጋር ህብረት በመፍጠር) በሚለው ክስ ላይ ግን ዐቃቤ- ሕግ የጸረ- ሽብር አዋጁን አንቀጽ 3 ከንዑስ አንቀጽ 1- 4 በመጥቀሱ ይህም ህግ በቅደም ተከተል በሽብርተኝነት ተግባር ሰው መግደልን፣ የሕብረተሰብን ደህንነት አደጋ ላይ መጣልን፣ እገታና ጠለፋን፣ በሽብርተኘነት ተግባር በንብረት ላይ ከፍተኛ አደጋ ማድረስን ስለሚጠቅስ እና በተጨባጭ በዐቃቤ- ሕግ የክስ ቻርጅ ላይ ምንም ዓይነት ይህን መሰል የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን የሚያሳይ ዝርዝር
ማስረጃ እና ማን ምን ዓይነት ወንጀል እንደፈጸመ የሚያመላክት ዝርዝር ማስረጃ  ባልቀረበበት ሁኔታ በድጋሚ የመንግሥትን ባለሥልጣናት ለመግደል፣ ባንኮችን ለመዝረፍና ህብረተሰቡን ለማሸበር የሚል ጨምረውበት እንዳለ  የበፊቱ መቅረቡን ተቃውመዋል፡፡

ዐቃቤ- ሕግ በበኩሉ እኛ ክሱን ያቀረብነው ሰው መግደል፣ ንብረት ማውደም ብለን ሳይሆን እነዚህን የወንጀል ተግባራት ለመፈጸም፣ ባለሥልጣናትን ለመግደልና ባንኮችን ለመዝረፍ እና ዜጎች እንዲሸበሩ ማደምና ማሴር በሚል ነው፣ ይህ የተፈጸመ ያለቀ ድርጊት አይደለም ነገር ግን ይህን ለመፈጸም የሥራ ክፍፍል ነው ያደረጉት በማለት ሊሻሻል የሚገባው ክስ አይደለም እላለሁ ብሏል፡፡

ፍርድ ቤቱ አራተኛው ክሥ ተቃውሞ እንዳልቀረበበት በመጥቀስ ያሳለፈው ሲሆን በአንደኛው ክሥ ላይ ግን የተከሳሽ ጠበቆች ተቃውሞ ቢያቀርቡበትም የዐቃቤ- ሕግ የክሥ ዝርዝር በጸረ-ሽብር አዋጁ አንቀጽ 3 ንዑስ
አንቀጽ 1- 6 ያለውን ነጥቦች ስንመለከት ክሱ ከቀረበበት የወንጀል ድርጊቶች- ማቀድን፣ ማሴርን፣ መዘጋጀትን የሚመለከት ስለሆነ የተከላካይ ጠበቆች ተቃውሞን ውድቅ አድርገነዋል ሲል ብይን ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ወዲያው የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ወደ ማድመጡ የገባ ሲሆን ተከሳሾች አቤቱታችን ይደመጥ ሲሉ  ባቀረቡት ሃሳብ ላይ ፍርድ ቤቱ በጽሑፍ አሳውቁ  ዛሬ ይሄን አላደምጥም በማለቱ ነታርከዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ- ሕግ ክሥን በተመለከተ የእምነት ክህደት ቃሉን የጠየቀው 1ኛ ተከሳሽ የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዷለም አራጌ ”ይህ በኢትዮጵያ ሠላማዊ ትግልን ማፈን
የተዘጋጀ የውሸት ድሪቶ ነው፤ እኔ ምንም አይነት ወንጀል አልፈጸምኩም …‘  ሲል ፍርድ ቤቱ  በመሐል ገብቶ  ዛሬ ሌላ ነገር ለመስማት ዝግጁ አይደለሁም፣ አሁን መናገር የምትችሉት ወንጀሉን ፈጽማችኋል ወይስ
አልፈጸማችሁም በቃ! ሲሉ አቶ አንዷለም ”ይገርማል እኔ ከዚህ በፊትም ፍርድ ቤት ቀርቤ አውቃለሁ፣ ነገር ግን ይህ ፍርድ ቤት ለእኛ ፍትህ ለመስጠት የቆመ አያስመስለውም፤ የገጠመንን ኢፍትሃዊነት በተናገርን ቁጥር በጽሑፍ አቅርቡ እየተባልን አድማጭ አጥተን እንገላታለን፣ መንግሥት እኛን በእሥር ላይ አድርጎ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን አኬልዳማ በሚል በሦስት ክፍል ፕሮግራም የሥም  ማጥፋት ዘመቻ እያካሄደብን ይገኛል፡፡‘ብሏል፡፡

ሁለተኛ ተከሳሽ የሆነው የአንድነት ፓርቲ አመራር አባል ናትናኤል መኮንን ”በሠላማዊ መንገድ መታገል ወንጀል ከሆነ አዎን ፈጽሜያለሁ፣ እንጂ የተባለውን የመንግሥት ድርሰት ግን አልፈጸምኩም፡፡‘ ያለ ሲሆን ሌሎች
ተከሳሾች የተባለውን ወንጀል አልፈጸምኩም እያሉ የመለሱ ሲሆን 5ተኛ ተከሳሽ ክንፈሚካኤል ደበበ በረደድ (አበበ ቀሲቶ) በበኩሉ ”ክቡር ፍርድ ቤት እዚህ የክሥ ቻርጅ ላይ የተዘረዘሩትን ተረታ ተረቶች አልፈጸምኩም፣ ወደፊትም አልፈጽምም፤ መንግሥት የእኛን ብቻ ሳይሆን የፍርድ ቤቱን ክብር ነው ያሳጣው- በፍርድ ቤት ሥራ ጣልቃ እየገባ‘ በማለት መልሥ ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾችን ክሱን ድርጊቱን ፈጽሜያለሁ ወይም አልፈጸምኩም ከሚል መልሥ በቀር ምንም እንዳይናገሩ ከገሰጸ በኋላ ዐቃቤ- ሕግ-ን ተከሳሾች ወንጀሉን አልፈጸምኩም ብለዋል  ምን ትላለህ በሚል ላቀረበው ጥያቄ ዐቃቤ- ሕግ ምንም እንኳ ተከሳሾች ክሱን ባይቀበሉትም  በክሥ ማመልከቻ ዝርዝር ላይ ያቀረብነው እንዲታይልን ቀጠሮ እንዲሰጠን እንጠይቃለን ብሏል፡፡

ፍርድ ቤቱም በውጭ አገራት ለሚገኙት ተከሳሾች በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጥሪ መሠረት ህዳር 27 ቀን 2004 ዓ.ም እንዲቀርቡ ቀጠሮ መያዙን አስታውቆ፣ በሀገር ውስጥ እሥር ቤት ለሚገኙት ስምንት ተከሳሾች ደግሞ
ታህሳስ 16 ቀን 2004 ዓ.ም ተለዋጭ ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቶ ችሎቱ ተበትኗል፡፡

የመለስ መንግስት አኬልዳማ ብሎ የሰራው እጅና እግር የሌለው የፈጠራ እንቶ ፈንቶ ድራማ ፣ መንግስት በምን ያክል ደረጃ መዝቀጡንና እንደ መንግስትነት  እንድናዬው ሳይሆን፣ ተራ ዱርዬም ከሚያስበው በታች የሚያስቡ ሰዎች ይህችን ታላቅ አገር እየገዙ መሆኑን ያሳያል ሲሉ አንድ የፍርድ ቤቱን ሂደት ለመከታተል የተገኙ ሰው ለዘጋቢያችን ገልጠዋል።

አቶ መለስ እራሳቸውን ከውርደት ለመታደግ ያሰሩት የፈጠራ ድራማ የህዝቡን ቁጣ መቀስቀሱም እየተነገረ
ነው።