የታሪክ ምሁሩ ጆን ማርካኪስ ህወሀት ከቀድሞው የደርግና የሀይለ ስላሴ ስርአቶች ለመማር ባለመቻሉ፣ ለመውደቅ ተቃርቧል አሉ

ህዳር 20 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-በኢትዮጵያ እና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ላይ መጽሀፎችን በመጻፍ እውቅና ያተረፉት ታወቂው የፖለቲካና ታሪክ ምሁር ጆን ማርካኪስ ፣ ህወሀት መራሹ መንግስት ከቀድሞው የደርግና የሀይለስላሴ ስርአቶች ለመማር ባለመቻሉ፣ ለመውደቅ ተቃርቧል አሉ።

“ኢትዮጵያ ፣ ዘ ላስት ቱ ፍሮንቲየርስ” የሚለውን አዲሱን መጽሀፋቸውን ለማስተዋወቅ በለንደን ቻትሀም ሀውስ በተገኙበት ወቅት እንደገለጡት አገዛዙ ስልጣን በበቂና ተጨባጭ በሆነ መልኩ ወደ ክልሎችና ወደ ወረዳዎች ለማስተላለፍ ባለመቻሉ ፣ የመፈረካከስ አደጋ ተጋርጦበታል።

ሌላው ታዋቂው ምሁር ፕሮፌሰር ክርስቶፈር ክላፋም የኢትዮጵያ መንግስት እጅግ አሳዛኝ የሆነ መንግስት ነው ብለውታል።

ኢትዮጵያ በውስጥና በአካባቢው ተጽኖ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አገደኛ ሁኔታ ውስጥ እንደምትገኝ የገለጡት ምሁሩ፣ ህወሀት እጅግ ፈላጭ ቆራጭ በሆነ መንገድ በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያደርገው ጥረት፣ የኢትዮጵያን መጻኢ እድል አደጋ ላይ ጥሎታል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ሁለቱ ምሁራን ያቀረቡት ጽሁፍ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት አክብሬያለው፣ ፌደራሊዝምን ተግባራዊ አደርጋለሁ፣ የኢትዮጵያን አንድነት ከመቼውም ጊዜ በላይ አስጠብቄያለሁ ለሚለው ኢህአዴግ፣
ትልቅ የዲፕሎማሲያዊ ውድቀት እንደሚያስከትልበት አስተያየቶች ቀርበዋል።

ፕሮፌሰር ክላፋም በእንግሊዞች ፖለቲከኞች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አላቸው ።