”ኦነግ ነፃ ድርጅት እንጂ የወያኔ ተለጣፊ ቡድን አይደለም” ሲል የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ገለጸ

ህዳር 21 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:- “የኦነግ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፤ ዛሬ ወያኔ ከኤርትራ መንግስት ጋር ያለው ግንኙነት ስለተቋረጠ የሚቋረጥ አይሆንም፤ኦነግ በሁለት እግሮቹ ራሱን ችሎ የቆመና የተመሰረተበትን ህዝባዊ አላማ በነፃነት የሚያራምድ ነፃ ድርጅት እንጂ፤የወያኔ ተለጣፊ ቡድን አይደለም”ሲል  የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ገለጸ።

“ኦነግ ኤርትራ ውስጥ ተመስርቶ ወደ ኢትዮጵያ የገባ እስኪመስል ድረስ፤የወያኔ ቡድን ስለ ኦነግ ባነሳ ቁጥር የኤርትራን ስም ሳያነሳ ያለፈበት ጊዜ የለም” ያለው የድርጅቱ የኢንፎርሜሽን ደስክ፤የኦነግ እንቅስቃሴ ባስደነበረው ቁጥር “ኤርትራ ነች የላከችብኝ” በማለት ራሱ ሳይቀር አሳምሮ የሚያውቀውን ሀቅ ለማዛባት በከንቱ እየደከመ እንደሚገኝም አመልክቷል።

“ኦነግ ውልደቱም ፣መሰረቱም እንቅስቃሴውም እዛው ወያኔ አፍንጫ ስር መሆኑን ራሱ ያውቀዋል ያለው” የግንባሩ መግለጫ፤ ከኤርትራ ጋር የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም በፀረ-ደርግ
ትግሉ ወቅት የተጀመረና የቆየ እንደሆነ አስረድቷል።

የኦነግ የኢንፎርሜሽን ዴስክ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ህዝብን ለማሸበር ታስቦ “አኬልዳማ”በሚል ርዕስ የተላለፈውን  የሽብር ፕሮፓጋንዳ አስመልክቶ ባወጣው በዚሁ መግለጫ፤የወያነ ሚዲያዎች ከመቼውም
ጊዜ በላይ በፀረ-ኦነግና መሰል ድርጅቶች  ፕሮፓጋንዳ የተጠመዱት፤በተቃዋሚ ድርጅቶች በተለይም በኦነግና ቄሮው የኦሮሞ ወጣት እንቅስቃሴ ስጋት ውስጥ ስለወደቀ ነው ብሏል።

“ወያነ ለምን ይህን ያህል ተሸብሮ ህዝብን ለማሸበር ተነሳ?” የሚለው ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ እንደሚሻና ምላሹም በሁለት ተያያዥ መልክ ሊቀመጥ  እንደሚችል የጠቀሰው ኦነግ፤የመጀመሪያው ምክንያት የተቃዋሚው ሀይል ትግል እንደ ሰደድ እሳት ስር ኣቱን ቀለበት ውስጥ አስገብቶ ቀስ በቀስ ሊውጠው እየተቃረበ መሆኑን በመረዳቱ የሚያሳየው የመንፈራገጥ ምልክት
ሊሆን ይችላል ብሏል።

“ሁለተኛውና ተያያዥ ምላሽ ሊሆን የሚችለው ደግሞ…”  ኦነግ እንዳለው፦ “ወያነ የብዙሀን ህዝቦች ድጋፍ የሌለው አናሳ ቡድን በመሆኑ ራሱ የተሸበረውን ያህል ተስፋ ያጣባቸውን ህዝቦች ማሸበር እንደ ብቸኛ አማራጭ ታይቶት ሊሆን ይችላል”

ኦነግ አያይዞም፦”ወያነ በተቃዋሚ ሀይሎቹ ትግል በስጋት ተውጦ እንደ ቡድን በግል መሸበሩ ተገቢ ነው።ነገር ግን ህዝቦች ከወያነ ጋር የሚሸበሩበት ምክንያት አይኖርም።ወያነ በጭራቅነት መስሏቸው ህዝቦችን ሊያስፈራራ የሚሞክርባቸው ድርጅቶች፤ከህዝቦቹ አብራክ የወጡና ለህዝቦች መብቶች መረጋገጥ የሚታገሉ ናቸውና”ብሏል።

“ወያነን የሚያሸብረው እንቅስቃሴ ለህዝቦች የምስራች ዜና እንጂ አስደንጋጭ መርዶ አይሆንም”ያለው ኦነግ፤ወያነን አስደንብሮ ሽብር እየለቀቀበት የሚገኘው ህዝባዊ ትግል፤ህዝቦች ከፋሽስታዊው ሥርዓት መንጋጋ ውስጥ እስከሚወጡ ድረስ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል።