(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 17/2010) የአብዲ ዒሌና የሽንሌ ዞን የሀገር ሽማግሌዎች ድርድር ያለውጤት ተበተነ::
አንድ ሳምንት የሞላውን ተቃውሞ ለማስቆም በአብዲ ዒሌ በኩል ግፊት የተደረገበት ድርድር የከሸፈው በእስር ላይ የሚገኙ ወጣቶች እንደማይፈቱ በመገለፁ ነው::
የክልሉን ምክትል ፕሬዝዳንት የላከው አብዲ ዒሌ በኮማንድ ፖስቱ የታሰሩ በመሆናቸው ልንፈታቸው አንችልም የሚል መልስ ለሽማግሌዎቹ ተነግሯቸል ::
ይህ በእንዲህ እንዳለም በሶማሌ ክልል ሽንሌ ዞን የተጀመረው ተቃውሞ መቀጠሉ ታውቋል::
ድርድሩ የተካሄደው በድሬዳዋ ከተማ ነው።
የሶማሌ ክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ አዲስ በሾሟቸው የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አማካኝነት ከሽንሌ የሀገር ሽማግሌዎች ጋር ዛሬ ድርድር የተቀመጡት ባልፈው ሳምንት የጀመረውን ህዝባዊ ንቅናቄ ለማስቆም መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
በድርድሩ ላይ በሀገር ሽማግሌዎቹ በኩል የቀረበው ቅድመ ሁኔታ በህዝባዊ ንቅናቄው ወቅት የታሰሩ የሶማሌ ወጣቶች ይፈቱ የሚል እንደነበር የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በአብዲ ዒሌ በኩል ለድርድር የቀረቡት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ወዲያውኑ መልስ መስጠት ባለመቻላቸው አዲስ አበባ ወደሚገኙት ወደ አቶ አብዲ ዒሌ ጋር በመደወል ያገኙትን ምላሽ ለሽማግሌዎቹ ያሳውቃሉ።
የአቶ አብዲ ዒሌ ምላሽ ወጣቶቹ የታሰሩት በኮማንድ ፖስቱ በመሆኑ እኛ መፍታት አንችልም የሚል ነበር።
ይህ ምላሽ ድርድሩ እንዳይቀጥል እንዳደረገው ነው የኢሳት ምንጮች የገለጹት።
በአብዲ ዒሌ በኩል የመጡት የክልሉ መንግስት ባለስልጣናት ያለቅድመ ሁኔታ ሽማግሌዎቹ ህዝባዊ ተቃውሞውን እንዲያስቆሙ በሃይለ ቃል ጭምር ሊያስፈራሩ ቢሞክሩም እንዳልተሳካላቸው ታውቋል።
እየተካሄደ ያለው ተቃውሞ ህገወጥ በመሆኑ ህዝቡ ተሳስቷል ብላችሁ በይፋ እንድትገልጹ የሚለው የባልስልጣናቱ ማስፈራሪያ ተቀባይነት በማጣቱም ድርድሩ ያለውጤት ሊበተን እንደቻለ ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
ይህ በእንዲ እንዳለም በሶማሌ ክልል የተጀመረው ህዝባዊ ተቃውሞ አድማሱን በማስፋት ወደ በርካታ አከባቢዎች መዛመቱን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
የተቃውሞ እምብርት የሆነው የሽንሌ ዞን አስተዳደር መዘጋቱ የታወቀ ሲሆን በአብዛኛው የዞኑ ወረዳዎች የመንግስት መዋቅር መፍረሱም ታውቋል።
ተቃውሞ በዚህ ሳምንት ወደ ደገሀቡር የዘለቀ ሲሆን ጂጂጋ ዙሪያ ባሉ የገጠር መንደሮች ተቃውሞ በመካሄድ ላይ መሆኑን የደርሰን ዜና አመልክቷል።
በጨካኝነቱ የሚታወቀው የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል ተቃውሞውን ለማፈን መጠነ ሰፊ ጥቃት የጀመረ ሲሆን በእስከአሁን 200 የሚደርሱ ወጣቶች በልዩ ሃይሉ ታፍነው ተወስደዋል።
የአብዲ ዒሌን ከስልጣን መውረድ በመጠየቅ እየተካሄደ ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞ የሚመሩት የሶማሌ ወጣቶች በርባራት ለኢትዮጵያ ህዝብ መልዕክት ያስተላልፉ ሲሆን ችግራችን ተመሳሳይ በመሆኑ ትግላችንም አንድ ላይ ይሆን ዘንድ አብረን እንነሳ ብለዋል።