ኢትዮጵያ የጋዜጠኞችን መብት በማክበር ረገድ 150ኛ ደረጃ ላይ ተቀመጠች

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 17/2010) ኢትዮጵያ የጋዜጠኞችን መብት በማክበር ረገድ ከአለም 180 ሀገራት ጋር ስትነጻጸር በ150ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ድንበር የለሽ የሪፖርተሮች ቡድን አመለከተ።

ፋይል

ድንበር የለሽ የሪፖርተሮች ቡድን የተባለ አለም አቀፍ ተቋም የየሃገራቱን የጋዜጠኞች መብት አከባበር አስመልክቶ ባወጣው የግምገማ ሪፖርት እንደገለጸው ኢትዮጵያ በአሸባሪነት ሰበብ ጋዜጠኞችን በማሳደድ የከፋ ርምጃ ትወስዳለች።

ኢትዮጵያ የጋዜጠኞችን መብት አከባበር በተመለከተ ከአመት አመት ሁኔታውን ከማሻሻል ይልቅ የባሰ ርምጃ እየወሰደች መሆኗን ሪፖርቱ አመልክቷል።

ድንበር የለሽ የሪፖርተሮች ቡድን የተባለው አለም አቀፍ ተቋም እንዳለው በኢትዮጵያ ያለው የጸረ ሽብር ሕግ የጋዜጠኞችን ድምጽ ለማፈን ዋነኛ መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

ሕጉ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2009 ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ በዚሁ ሰበብ የተከሰሱ ጋዜጠኞች ረጅም አመት በእስር የማቀቁበት ሁኔታ ተከስቷል።

የተወሰኑ በፍርድ ሲታሰሩ ሌሎች ደግሞ ያለሕጋዊ ሒደት ዘብጥያ የሚወርዱበት ሁኔታ አሁንም እንዳለ ሪፖርተር ዊዝ አውት ቦርደር የተባለው ተቋም አጋልጧል።

እናም ሪፖርቱ 180 ሃገራትን በማነጻጸር ባሰፈረው የጋዜጠኞች መብት አያያዝ የግምገማ ውጤት ኢትዮጵያ በዘንድሮው የ2018 አመት 150ኛ ደረጃ ላይ መሆኗን ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።

እንደ ድንበር የለሹ የሪፖርተሮች ቡድን ሪፖርት መሰረት ኢትዮጵያ በ2016 ያላት ድርሻ 142 ስለነበር ከዘንድሮው ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ነበር።

አሁንም ግን በጋዜጠኞች አያያዝ ኢትዮጵያ የባሰ ደረጃ ላይ ትገኛለች ነው ያለው።

ኢትዮጵያ በቅርቡ የተወሰኑ ጋዜጠኞችን ከእስር ብትፈታም በሃገሪቱ አሁንም የፕሬስ ነጻነት እንደሌለ ድንበር የለሽ ሪፖርተሮች ቡድን አረጋግጧል።

እንደ ሪፖርቱ ገለጻ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2014 የተዘጉ 6 የፕሬስ ውጤቶች አሁንም ፈቃዳቸው አልተመለሰም።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም 30 ጋዜጠኞች መሰደዳቸውም የዚሁ ችግር ማሳያ ነው ብሏል።

አሁን በሀገሪቱ ባለው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተወሰኑ የብሮድካስት መገናኛ ብዙሃንን ማየትና መስማት ክልክል ነው።

ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃኑን ሕዝቡ እንዳይከታተልም ኢንተርኔት በተደጋጋሚ እንደሚቋረጥ ሪፖርቱ አመልክቷል።