የአቡነ ናትናኤልን ጥረት የሚያሰናክሉ ወገኖች መነሳታቸው

ህዳር 4 (አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች መካከል ዕርቅን ለማውረድ የሚደረገው ጥረት በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት የአቡነ ናትናኤልን ጥረት የሚያሰናክሉ ወገኖች መነሳታቸው ተሰምቷል። በዚህም የተነሳ አቡነ ናትናኤል በሳምንቱ መጨረሻ ወደ ሐገረ ሥብከታቸው መሄዳቸውን ከአዲስ አበባ የመጣው ዜና ያስረዳል።

የቤተክርስቲያኒቱን አንድነት አጥብቀው ይሻሉ የሚባሉት ዓቃቢ መንበር ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ወደ ሠላም በሚወስደው መንገድ ላይ የሚያደርጉት ጥረት በአንዳንዶች ዘንድ አልተወደደም።

ከሲኖዶሱ ዕውቅና ውጭ በራስዎ እየተንቀሳቀሱ ነው ከሚለው ወቀሳ ጀምሮ አቡነ መርቆሪዎስን አንፈልግም እስከሚለው ድረስ ከመንግስት ጋር ቅርበት ጳጳሳትና ለሎች ወገኖች ችግር የፈጠሩ መሆናቸው ተመልክቷል።

በዚህም መሠረት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ባለፈው አርብ ወደ አርሲ ሐገረ ስብከት መመለሳቸው ተሠጥቷል በርሳቸው ሰብሳቢነት ይካሄዳሉ የተባሉ ስብሰባዎችም ተሰርዘዋል።

ዓቃቤ መንበር ብፁዕ አቡነ ናትናኤል እና በርካታ ጳጳሳት በፁዕ አቡነ መርቆሪዎስ በመንበራቸው እንዲቀመጡና የቤተክርስቲያኒቱ አንድነት እንዲመለስ ቢፈልጉም መንግስት አዲስ ፓትርያርክ እንዲመርጡ እየገፋ መሆኑም እየተሰማ ነው ብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዎስና ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በቀዳሚነት መሰለፋቸው ተሰምቷል  አቡነ ሳሙኤልንም ለማሾም የሚሮጡ ወገኖች መኖራቸው እየተገለፀ ነው። መንበረ ፓትሪያርክነቱ በርስትነት በአንድ አከባቢ ተወላጆች ሥር ቀጠለ የሚለውን ትችት ለመከላከል ብፁዕ አቡነ ገሪማ በርቀት በአማራጭነት ሥለመያዛቸውም እየተነገረ ነው።