የአሜሪካ ደምጽ ራዲዮ ዘጋቢ ፒተር ሀይንላይን ታሰረ

ግንቦት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ጋዜጠኛ ፒተር ሀይንላይን የታሰረው ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ዛሬ በአወልያ ያደረጉትን ተቃውሞ ለመዘገብ በሄደበት ጊዜ ነው ። ፒተር ከአዲስ አበባ በሚያስተላልፋቸው ነጻ ዘገባዎቹ በመላው የአሜሪካ ድምጽ አድማጮች ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ተቀባይነት አለው። በያዝነው ሳምንት መግቢያ ላይ ጋዜጠኛ ፒተር የሙስሊሞችን ተቃውሞ በመዳሰስ የሰራው ዘገባ ለእስራቱ አፋጣኝ ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚሉ አስተያየቶች ይቀርባሉ።

የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆኑት ካይል ካይሊንግ ፣ የጋዜጠኛውን መታሰር አረጋግጠዋል። የመለስ መንግስት ጋዜጠኞቻቸው ስራቸውን በተገቢው መንገድ እንዲያከናውኑ ሁኔታዎችን ምቹ ማድረግ እንደሚገባው ሃለፊው ተናግረዋል። ሚስተር ካይል ለጋዜጠኞቻችን ደህንነት ቅድሚያ የምንሰጥ በመሆኑ፣ ተጨማሪ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ጥረት በማድረግ ላይ ነን ሲልም አክለዋል።

ምንጮች እንደሚሉት የዛሬውን ተቃውሞ ለመዘገብ ወደ አወልያ የሄዱ ሌሎች የውጭ አገር ጋዜጠኞችም ሲቪል በለበሱ የደህንነት ሀይሎች ተዋክበው ከአካባቢው እንዲባረሩ ተደርጓል። የመለስ መንግስት ሁለት የስዊድን ጋዜጠኞች እና ሶስት ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኞችን  በሽብርተኝነት ከሶ ለእስር መዳረጉ በአለም አቀፍ ደረጃ እያስወገዘው ባለበት በአሁኑ ሰአት እንዲህ አይነት እርምጃ መውሰዱ አገዛዙ የገባበትን አጣብቂኝ ያሳያል ተብሎአል።

አቶ መለስ በቡድን 8 ስብሰባ ላይ ተገኝነተው በተመለሱ ማግስት ጋዜጠኛ ፒተር ሀይላይን እንዲታሰር ማድረጋቸው ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሆኗል። የጋዜጠኛ ፒተር መታሰር በአሜሪካ እና በመለስ መንግስት መካከል ከፍተኛ ውዝግብ ይፈጥራል ተብሎ ይገመታል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide