በአዲስ አበባ አትክልት ተራ ፤ፖሊሶች ከነጋዴዎች እና ከነዋሪዎች ጋር ተጋጩ

ግንቦት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ትናንት ፣ መጋቢት 16፣ 2004ዓም በአትክልት ተራ ፖሊሶች አንድ አትክልት ሻጭን መደብደባቸውን ተከትሎ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ተቃውሞ በማሰማቸው  ፖሊሶች ወደ ሀይል እርምጃ አምርተዋል።

በተከራይ እና አከራይ  መካከል የተነሳን ውዝግብ ሳቢያ  በጉሊት ሽያጭ የሚተዳደር ሰኢድ ኡመካ የተባለ ወጣት በፖሊሶች በመደብደቡ፤ የአፍሪካ አንድነት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተቃውሞአቸውን በጩኸት አሰምተዋል።

ጩኸቱ ወደተካረረ ፍጥጫ አምርቶ ግጭት ማስከተሉን የገለጹት የዜናው ምንጮች፤ ነዋሪዎች ከፖሊሶች ጋር በፈጠሩት በዚሁ ግብግብ ፖሊሶችን ጨምሮ የአካባቢው ነጋዴዎች እና ሸማቾች ጉዳት እንደደረሰባቸው እና ከ15 ያላነሱ ሰዎችም ለእስር እንደተዳረጉ አመልክተዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በመርካቶ በንግድ ሥራ ውስጥ ከተሰማሩት ወገኖች መካከል 75 በመቶ ያህሉ ሕገወጥ ናቸው በሚል አዲስ ዘመቻ ለመክፈት መዘጋጀቱን ምንጮች ጠቆሙ፡፡

ባለሥልጣኑ በጥናት ደርሼበታለሁ ባለው መሰረት በመርካቶ ሕጋዊ ንግድ ፈቃድ አውጥተው የሚሰሩ ነጋዴዎች ቁጥር 25 በመቶ ብቻ ሲሆኑ የተቀሩት 75 በመቶ ያህሉ ንግድ ፈቃድ የሌላቸውና ግብርም የማይከፍሉ ናቸው ብሏል፡፡

ጥናቱ አያይዞም በሃገሪቱ ካለው አጠቃላይ የገንዘብ ልውውጥ ግማሸ ያህሉን የሚይዘው የመርካቶ አካባቢ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

ከዚሁ ጥናት ጋር በተያያዘም ባለሥልጣኑ “የመርካቶ ፕሮጀክት” በሚል በመርካቶ አካባቢ ሁለት ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች እና አሰር የታክስ ማዕከላትን ከፍቷል፡፡

በጉዳዩ ላይ አስተያየት የተጠየቁ አንድ በመርካቶ አካባቢ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴ እንደተናገሩት በአካባቢው ንግድ ፈቃድ አላወጡም የሚባሉት መንገድ ላይ ከፖሊስ ጋር ግብግብ ገጥመው የእለት ግርሳቸውን የሚሸፍኑ አነስተኛና ጥቃቅን ነጋዴዎች ሁሉ ተቆጥረው መሆኑን አስታውሰው እነዚህ ወገኖች ግብር ክፈሉ ብሎ ማሳደድ ደሃው ሕዝብ ትንሸ ነገር ሰርቶ እንኳን እንዳያድር ከማድረግ ያለፈ ፋይዳ የለውም በማለት የባለስልጣኑን እርምጃ ተቃውመዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ባለፈው ዓመት ከ51 ቢሊየን ብር በላይ ግብር መሰብሰብ የቻለ ሲሆን ዘንድሮ 76 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ቢያቅድም ባለፉት አስር ወራት ብቻ መሰብሰብ የቻለው 59 ቢሊየን ብር ገደማ መሆኑ ጋር ሲነጻጸር በቀሪ ሁለት ወራት ዕቅዱን የማሳካቱ ነገር ጥያቄ ምልክት ውስጥ ያለ ነው፡፡የመርካቶ ፕሮጀክት የባለሥልጣኑን እጅግ የተጋነነ የገቢ ዕቅድ ለማሳካት ሊጠቅመው ይችላል ተብሏል::

ባለሥልጣነ  አምና በደረጃ “ሐ” ሥር ያሉ አነስተኛ ነጋዴዎችን በተመለከተ አጠናሁት ባለው ጥናት መሰረት ደረጃቸውን በድንገት በማሳደጉ አነስተኛና ጥቃቅን ንግድ ላይ የተሰማሩ ወገኖች ጭምር በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ግብር እንዲከፍሉ መጠየቃቸው ከፍተኛ ተቃውሞን ቀስቅሶበት እንደነበር ያታወሳል፡፡በተጨማሪም አምስት ሺ ብር የማይሞላ ካፒታል ያላቸው ወገኖች ጭምር ካሸ ሬጅስተር የተባለውን ማሸን ከብር ስምንት ሺ በላይ አውጥተው እንዲገዙ መጠየቃቸውም እንዲሁ ተመሳሳይ ተቃውሞን አስነስቶበት ነበር፡፡ባለሥልጣኑ ገቢን ለማሳደግ ብቻ የያዘው ሩጫ ከበርካታ ነጋዴዎች ጋር እያላተመው እንደሚገኝም ይታወቃል፡፡

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide