(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 9/2010)
በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ የጉዞ ማስጠንቀቂያ አወጣ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ተመሳሳይ መግለጫ ማውጣቱ ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ በኢትዮጵያ ለአሜሪካ አምባሳደር ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ባወጣው የቅድመ ማስጠንቀቂያ መግለጫ ሰራተኞቹ ከአዲስ አበባ ውጪ በምንም አይነት መንቀሳቀስ አደገኛ ሁኔታን ሊያስከትል ይችላል ብሏል።
እናም በሀገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን የሚሰጡትን መረጃ በመከታተል ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋልም ነው ያለው።
በኤምባሲው መግለጫ መሰረት በኢትዮጵያ የተቃውሞ ሰልፎችና ሕዝባዊ አመጾች ድንገት ሊቀሰቀሱ ይችላሉ።
በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ የሀገሪቱ ቀውስ ሊባባስ እንደሚችል ነው ያስጠነቀቀው።
በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ ያወጣውን የቅድመ ማስጠንቀቂያ መግለጫ መነሻ በማድረግም የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ተመሳሳይ ማሳሰቢያ መስጠቱ ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአዲስ አበባ ከአሜሪካው አምባሳደር ማይክል ሬይነር ጋር በሀገሪቱ ባለው አሳሳቢ ሁኔታ ላይ መምከራቸው ተነግሯል።
አቶ ደመቀ አምባሳደሩን በጽሕፈት ቤታቸው ለማናገር የተገደዱት አሜሪካ የኢትዮጵያ ጉዳይ በእጅጉ ያሳሰባት በመሆኑ ነው ተብሏል።
በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በኩል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመደንገግ ስብሰባ ላይ መሆኑ ይነገራል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለ3 ወራት ወይም ለ6 ወራት ሊደነገግ እንደሚችል ዘገባዎች አመልክተዋል።