ሁለት የአገዛዙ የጸጥታ ሃይሎች ተገድለው ተገኙ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 9/2010)

በባህር ዳር ሁለት የአገዛዙ የጸጥታ ሃይሎች ተገድለው ተገኙ።

በደብረታቦር በውስጣዊ አሰራር የሰዓት እላፊ ቁጥጥር ተደርጓል።

ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኋላ የተገኘ ማንኛውም እግረኛና ተሽከርካሪ ፍተሻ እንደሚደረግለትም ታውቋል።

በሌላ ዜና በመተሀራ ትላንት የቦንብ ጥቃት ተፈጽሟል ።

በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ዛሬም የተቃውሞ ሰልፎች ሲደረጉ እንደነበር የደረሰን መረጃ ይጠቁማል።

ባህርዳር በዚህ ሳምንት በተለየ ወታደራዊ ጥበቃ ስር መቆየቷን ተከትሎ ትላንት ምሽት የተፈጸመው ግድያ በአገዛዙ ዘንድ ድንጋጤን መፍጠሩን የኢሳት የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።

ሁለት የአገዛዙ የጸጥታ ባልደረቦች የተገደሉት በባህርዳር ከተማ በተለያዩ መንደሮች መሆኑ ታውቋል።

አገዳደላቸው ተመሳሳይ መሆኑ ደግሞ ግድያው ታቅዶበት በአንድ ሃይል ለመፈጸሙ ማረጋገጫ የሚሰጥ ነው ይላሉ የመረጃ ምንጮቹ።

አንደኛው የፌደራል ፖሊስ አባል የተገደለው በባህርዳር ትልቁ ስታዲየም አካባቢ ሲሆን ሁለተኛው የደህንነት ባልደረባ ደግሞ ኪቤአድ በሚባለው መንደር መሆኑ ታውቋል።

ዛሬ ጠዋት አስክሬናቸው የተገኘው ሁለቱ የጸጥታ አባላት የአገዳደላቸው ሁኔታ ተመሳሳይ መሆኑ ያስደነገጠው አገዛዙ የተለየ ምርመራ እያደረገበት ሲሆን ግድያውን የፈጸሙትን ለመያዝ አሰሳ መጀመሩን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

የሁለቱን የጸጥታ አባላትን ግድያ የፈጸመው አካል ማን እንደሆነ የታወቀ ነገር የለም።

ትላንት በሸዋ ሮቢት በታጠቁ ሃይሎች 3 የአጋዚ ወታደሮች መገደላቸውን መዘገባች የሚታወስ ነው።

በሌላ በኩል ደብረታቦር በይፋ ባልተገለጸ የሰዓት እላፊ አዋጅ ስር መውደቋን ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቷል።

ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኋላ ማንኛውም የሚንቀሳቀስ እገረኛና ተሽከርካሪ የሚፈተሽ መሆኑን የገለጹት የኢሳት የመረጃ ምንጮች ምክንያቱ ምን እንደሆነ አይታወቅም ብለዋል።

ከአንድ ሰዓት በኋላ መንገድ ላይ የሚታይ ይታሰራል ያሉት ምንጮች ላለፉት ሶስት ቀናት ተግባራዊ መደረጉን ጠቅሰዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአንዳንድ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ዛሬም ተቃውሞ መደረጉን የተለያዩ የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።

በሻሸመኔ፣በአርሲ ነገሌና በጉደር ህዝባዊ ተቃውሞዎች የተደረጉ ሲሆን በአርሲ ኢተያ ግጭት መከሰቱን ለማወቅ ተችሏል።

የኢተያው ግጭት በአገዛዙ ካድሬዎች የተቀሰቀሰ በመሆኑ ህዝቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል።

በተመሳሳይ ትላንት በመተሃራ አዲስ ከተማ ሃሙስ ገበያ ቦንብ ተወርውሮ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

የአካባቢው የኢሳት ምንጮች እንደሚሉት በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ የእርስ በእርስ ግጭት ለመፍጠር በሚል የወረወረው ቦምብ በመሆኑ ህዝብ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል።

በሌላ ዜና አዲስ አበባ ላይ ከፍተኛ የቤንዚን እጥረት ተከስቷል::

በሰሞኑ ተቃውሞ መንገዶች በመዘጋታቸው ምንም ነዳጅ እንዳይገባ ሆኗል።

በመጠባበቂያ የተቀመጠው ነዳጅ አልቋል::

በአሁን ሰአት ነዳጅ ማደያዎች ላይ ረጅም የመኪና ሰልፍ ይታያል።

በሌላ በኩል የዶላር እጥረት አስመጭዎችን በንግድ ስራው በኩል ተስፋ ያስቆረጠበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

የገበያ መረጋጋት የለም፡፡ የእቃዎች ዋጋ በጣም ንሯል።

ትላልቅ ድርጅቶች በተለይ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች በርካታ ሰራተኞችን ከስራ እየቀነሱ ነው::