በኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ መዝገብ ላይ ብይን ይሰጣል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 9/2010)

የአማራ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጎንደር ምድብ ችሎት በኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ መዝገብ ላይ ብይን ለመስጠት የመጨረሻ ቀጠሮ መስጠቱ ተሰማ ።

በጎንደር የተሰየመው ችሎት በኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ መዝገብ ላይ “የከላከሉ፣አይከላከሉ” በሚለው ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ይዞ እንደነበርም ታውቋል።

በጎንደር ዛሬ የተሰየመው ችሎት በኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የክስ መዝገብ ላይ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን ማስረጃ ይመረምራል።

መርምሮም “ይከላከሉ፣ አይከላከሉ” የሚለውን ብይን ይሰጣል ተብሎ ነበር።

ነገር ግን ችሎቱ ከጉዳዩ ስፋት አንፃር እያንዳንዱ ዳኛ ጉዳዩን ሊመለከተው ይገባል በሚል ለየካቲት 22/2010  ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ታውቋል።

ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮውን ሲሰጥ ብይኑን ለማጠቃለል ነው መዝገቡን መመልከት ያለብኝ ማለቱ ተሰምቷል።

የጠቅላይ አቃቤ ሕግን የወከሉትና የተከራከሩት አቶ አንተነህ አያሌው በርካታ መዝገቦች ስላላቸው ቀጠሮው ለመጋቢት ወር አጋማሽ እንዲራዘምላችው ጠይቀው ነበርም ተብሏል።

ፍርድ ቤቱ ግን ጊዜ ማባከን ነው በሚል ረጅም ቀጠሮ አልሰጥም በማለት የሁለት ሳምንት ቀነ ቀጠሮ አስቀምጧል።

የኮለኔል ደመቀ ዘውዱ ጠበቃ አቶ አለለኝ ምህረቱ “ፍርድ ቤቱ በቀጣይ ቀጠሮ ብይን የሚሰጠው በመዝገቡ ላይ ነው? ወይንስ በመዝገቡ ላይ ባቀረብናቸው መቃወሚያዎች ነው?” የሚል ጥያቄ አቅርበዋል።

ለዚህም ፍርድ ቤቱ በመዝገቡ ላይ ግራ ቀኛችሁ የምትሰጡት አስተያየት አብቅቷል።–ቀጠሮው በዋናነት በመዝገቡ ላይ ብይን ለመስጠት ነው ሲል ምላሹን ሰጥቷል።

በሌላ በኩል ኮለኔል ደመቀ ዘውዱ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዳልተያዙ በመግለፅ፣ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተያዙ የተባሉበት መዝገብ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ እንዲልክ ቢጠየቅም እስካሁን አለመላኩም በችሎቱ ላይ ተነስቷል ።

በተመሳሳይ የደህንነት መስሪያ ቤቱ ክሱ ላይ የኮሎኔል ደመቀ የስልክ ንግግር ነው ብሎ በፅሑፍ ያያዘውን ማስረጃ በድምጽ አስደግፎ እንዲልክ ቢታዘዝም አላቀረበም ብሏል መረጃው።

የመዝገብ ቁጥሩም ቢሆን የሌላ ግለሰብ መሆኑንና ከተዘጋም መቆየቱን በመግለጽ የቀረበባቸው ማስረጃ  የሀሰት ሰነድ ነው በማለት መከራከራቸውም ተሰምቷል።