(ኢሳት ዲሲ–ጥር 9/2010)
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በብዛት የተበላሸ ብድር ያላቸው ድርጅቶች ሰፋፊ የእርሻ ፕሮጀክቶችና የቱርክ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የሆነው አይካ አዲስ መሆኑን አስታወቀ።
በባንኩ ከፍተኛ የተበላሸ ብድር እንዳለበት የሚታወቀውና የህወሃት ንብረት የሆነው ኤፈርት ግን በዚህ ዝርዝር ውስጥ አልተካተተም።
የህወሃት ንብረት የሆነው ሬዲዮ ፋና የባንኩን ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ክፍሌ ሃይለየሱስን ጠቅሶ እንደዘገበው የልማት ባንክ በተለያዩ ዘርፎች ብድር ሰጥቶ አደጋ ውስጥ ያለውን ብድር ለማስመለስ ግብረ ሃይል አቋቁሟል።
ልማት ባንኩ ከሰጠው በድር ውስጥ 8 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የተበላሸ እንደሆነም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
የተበላሸ ብድር ያለበት ደረጃ ችግር ውስጥ በመሆኑ የማስመለሱ ነገር ላባንኩ ህልውና ውሳኝ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል ሪፖርተር ያናገራቸው የልማት ባንኩ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተሾመ አለማየሁ የቱርኩ አይካ አዲስ ጨርቃ ጨርቅና ሌሎች ትላልቅ ኢንቨስትመንቶች እንዲሁም የሰፋፊ እርሻ ፕሮጀክቶች በብዛት የተበላሸ ብድር ያለባቸው ናቸው ብለዋል።
ልማት ባንኩ በአጠቃላይ ካበደረው ገንዘብ ውስጥ 8 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የተበላሸ ብድር እንደሆነ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
ከዚህ ውስጥ 3 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የሚሆነው የሰፋፊ እርሻ ፕሮጀክቶች ሲሆን ቀሪው ብዙ የተነገረለት የቱርኩ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ አይካ አዲስና ሌሎች የፋብሪካ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሌሎች የፋብሪካ ፕሮጀክቶች የተባሉት ውስጥ የሕወሃት ንብረት የሆነው ኤፈርት መኖርና አለመኖሩ የተጠቀሰ ነገር የለም።
ኢሳት ያናገራቸው የዘርፉ ሙያተኞች ልማት ባንኩ የተበላሸ ብድር ብሎ የገለጸው መጠን አስደንጋጭ ቢሆንም ከተጠቀሰው በላይ እንደሆነም ተናግረዋል።
የኤፈርት ንብረት የሆኑት አልመዳ ጨርቃ ጨርቅ፣አዲስ መድሃኒት ፋብሪካና መሶበ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከ21 አመት በፊት የወሰዱት ብድር ወለዱን ጨምሮ ከ14 ቢሊየን ብር በላይ ደርሷል ብለዋል።
ሆኖም ይሄ ብድር የተበላሸ በመባሉ እንዳይከፈል መደረጉን ሙያተኞቹ ገልጸዋል።
ባንኩ ያቋቋመው ግብረ ሃይል እስከ ሐራጅና ሌሎች ርምጃዎች እወስዳለሁ የሚል ቁርጠኝነት ካለው ከእነዚህ የኤፈርት ኩባንያዎች መጀመር እንዳለበት ጨምረው ተናግረዋል።