ሰሜንና ደቡብ ኮሪያ በአንድ ባንዲራ የኦሎምፒክ ውድድር ሊሳተፉ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 9/2010)

ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በጠላትነት የሚተያዩት ሰሜንና ደቡብ ኮሪያ በአንድ ባንዲራ በአለም አቀፍ የኦሎምፒክ ውድድር ለመሳተፍ መስማማታቸው ተዘገበ።

በአንዲት ኮሪያ ስም ሁለቱ ሀገራት ለመወዳደር መስማማታቸውን በሰበር ዜና የዘገበው የብሪታኒያው የዜና ማሰራጫ ቢቢሲ በቀጣዩ ወር በሚካሄደው የክረምት ኦሎምፒክ ስምምነታቸው ተግባራዊ እንደሚሆንም አመልክቷል።

ሰሜንና ደቡብ ኮሪያ በክረምቱ ኦሎምፒክ በአንድ ኮሪያ ስም በጋራ ባንዲራ ለመወዳደር ከመስማማታቸው ባሻገር በአንዳንድ ውድድሮች የጋራ ቡድን ለመመስረት መስማማታቸውም ተመልክቷል።

ሁለቱ ሀገራት በበረዶ ላይ የሚደረገውን ጨዋታ ማለትም ሆኪ በጋራ በአንድ ቡድን ለመሰለፍ መወሰናቸውን የደቡብ ኮሪያ የሆኪ አሰልጣኞችና ወግ አጥባቂ ጋዜጠኞች የማሸነፍ እድላችንን ይገታዋል በማለት በመቃወም ላይ መሆናቸው ታውቋል።

አለም አቀፉ የክረምት ኦሎምፒክ የሚካሄደው በዚያው በደቡብ ኮሪያ ፒዮንግ ቻንግ በተባለ ግዛት ሲሆን እንደ አውሮፓውያኑ ከየካቲት 9 እስከ 27 እንደሚካሄድም ታውቋል።

በኒዮክለር የጦር መሳሪያዎቼ የአሜሪካ ከተሞችን ማጥፋት እችላለሁ በማለት ስትዝት የቆየችው ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካ ወዳጅ ደቡብ ኮሪያ ጋር የፈጠረችው ግንኙነት ያልተጠበቀ ሆኗል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጥር ከ1910 ጀምሮ እስከ ሁለተኛው የአለም ጦርነት በጃፓን ንጉሳዊ አገዛዝ ስር የቆየችው ኮሪያ የሁለተኛውን የአለም ጦርነት ተከትሎ በጃፓን በደረሰባት ሽንፈት ሰሜኑን የኮሪያ ክፍል ያያኔዋ ሶቭየት ህብረት ስትይዝ ደቡባዊን ክፍል ደግሞ አሜሪካ ተቆጣጠረች።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1948 ኮሪያ በይፋ ሁለት ሀገር ሆና ተከፈለች።

በሃያላኑ ሀገራት ተጽእኖ ስር የወደቁትና ሰሜንና ደቡብ በሚል ሁለት ቦታ የተከፈሉት ደቡብ ኮሪያውያን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከሰኔ 25/1950 እስከ ሐምሌ 27/1953 ለሶስት አመታት በጦርነት ውስጥ ቆይተዋል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 70 አመታት ያህል በጠላትነት ውስጥ የቆዩት ሰሜንና ደቡብ ኮሪያ ከአንድ ብሔረሰብ የወጡና ተመሳሳይ ቋንቋ የሚናገሩ ህዝቦች ናቸው።

የደቡብ ኮሪያ ህዝብ ብዛት 52 ሚሊየን ያህል ሲሆን ሰሜን ኮሪያውን ደግሞ 26 ሚሊየን ናቸው።