(ኢሳት ዲሲ–የካቲት/2011)የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ለተፈናቀሉ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ መላክ ጀመረ።
ኮሚሽኑ በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ለተፈናቀሉ ዜጎች የተለያዩ ሰብዓዊ ድጋፎች መላክ መጀመሩን አስታወቋል።
በአማራ ክልል ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ከ90 ሺህ ባላይ ዜጎች በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ።
ከእነዚህ ተፈናቃይ ዜጎች ውስጥም አብዛኛዎቹ በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር የተፈናቀሉ ዜጎች መሆናቸው ነው የተገለፀው።
በአሁኑ ወቅትም ከሁለቱ ዞኖች የተፈናቀሉ ከ45 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች በ13 ጊዜያዊ መጠለያ ካምፖች የሚገኙ መሆኑን የክልሉ መንግስት አስታውቋል።
ዘገባዎች እንዳመለከቱት በተለያዩ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃይ ዜጎች አስፈላጊው የሰብዓዊ እርዳታ እየደረሳቸው አለመሆኑን ለመመልከት ችሏል።
በተለይም በአይምባ፣ ሳንጃ እና ትክል ድንጋይ የሚላኩ ድጋፎች በፍጥነት እንደማይደርሱና ከምግብ ባሻገር የጤና አገልግሎት የማግኘት ችግር አለ ተብሏል ።
በብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የአቅርቦትና ሎጅስቲክ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አይድሩስ ሀሰን በጎንደር እና አካባቢው መፈናቀል ሲከሰት ይህ ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑን ገልጸዋል ።
በ1ኛ ዙር እና ሁለተኛ ዙር ለተፈናቀሉ 10 ሺህ ገደማ ዜጎች ኮሚሽኑ ከክልሉ በቀረበለት ጥያቄ መሰረት ድጋፍ አድርጓል ነው ያሉት።
ለ3ኛ ዙር ተፈናቃዮች ኮሚሽኑ አፋጣኝ ምላሽ ያልሰጠው ክልሉ ጥያቄውን በፍጥነት ባለማሳወቁ መሆኑን አብራርተዋል።
አሁን ላይም ክልሉ ለ45 ሺህ 922 ለሚሆኑ ተፈናቃዮች አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲደረግለት ከሚሽኑን ጠይቋል ብለዋል።
በዚህም መሰረት ኮሚሽኑ ከዛሬ ጀምሮ አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፎችን ወደ ቦታው ማጓጓዝ መጀመሩን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
የሰብዓዊ እርዳታዎችም የምግብ ነክ ድጋፎችን ጨምሮ የምግብ ማብሰያዎች፣ ብርድ ልብስ እና ሌሎች አልባሳት እንዲሁም ቁሳቁሶች መሆናቸው ነው የተገለፀው።