የማረሚያ ቤት የፖሊስ አባላት ላይ ክስ ተመሰረተ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 13/2011)ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ላይ በደረሰው ቃጠሎ በተነሳው ረብሻ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል በሚል የተጠረጠሩ የማረሚያ ቤት የፖሊስ አባላት ላይ ክስ ተመሰረተ።

ተከሳሾች በፌደራል ማረሚያ ቤቶች የቂሊንጦ፣ የዝዋይ እና የሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት በተለያየ የሃላፊነት ደረጃ ሲሰሩ የነበሩ መሆናቸውም ተገልጿል።

ፋይል

የክሱ ዝርዝር እንደሚያስረዳው ነሃሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም ጠዋት በፌደራል ማረሚያ ቤቶች ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ላይ በደረሰው ቃጠሎ በተነሳው ረብሻ ምክንያት ከኃላፊዎች በተሰጠ ትዕዛዝ በማረሚያ ቤት የፖሊስ አባላት በተተኮሰ ጥይት በታራሚዎች ላይ ከባድ አካላዊ ጉዳትና ህይወታቸው እንዲያልፍ ተደርጓል።

ተከሳሾች ኦፊሰር ገብረማርያም ወልዳይ አብርሃ፣ ሱፐር ኢንተንደንት አስገለ ወልደጊዮርጊስ ወልደማርያም፣ ዋና ሱፐር ኢንተንደንት  አሰፋ ኪዳኔ ተድላ፣ ሱፐር ኢንተንደንት ገብረእግዚአብሄር ገብረ ሃዋርያት፣ ሱፐር ኢንተንደንት ተክላይ ሀይሉ ተክለ ሃይማኖት፣ ሱፐር ኢንተንደንት አቡ ግርማ ወልደሚካኤል፣ ሱፐር ኢንተንደንት አዳነ ሀጎስ ህሻ እና ሱፐር ኢንተንደንት ገብራት መኮንን ገብሩ ናቸው።

በክሱ እንደተመለከተው በማረሚያ ቤት ቃጠሎ ምክንያት ከ400 በላይ የሚሆኑ ታራሚዎችን ወደ ሸዋሮቢት ተሃድሶ ልማት ማረሚያ ቤት እንዲወሰዱ ተደርገዋል ።

በዚሁ ጊዜም የነበራቸውን ንብረት በመቀበል በባዶ እግራቸው በቁምጣ ብቻ በተሽከርካሪ ላይ እንዲጫኑ በማድረግ፤ ሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት ሲደርሱም በመስመር በማሰለፍና በማረሚያ ቤት ፖሊስ አባላት በዱላ ተደብድበዋል ነው የተባለው።

175 የሚሆኑ ታራሚዎችን ደግሞ ባዶ ቤት የሲሚንቶ ወለል ላይ እንዲተኙ በማድረግ፣ ለሁለት ለሁለት በካቴና በማሰር ለረዥም ጊዜ በማቆየትና በባዶ እግራቸው ሽንት ቤት እንዲጠቀሙ በማስደረግ፣ እጃቸውን ሳይታጠቡ ምግብ እንዲመገቡ እና ህክምና በመከልከል እንዲሁም ከቤተሰብ ጋር እንዳይገናኙ አድርገዋል ይላል ክሱ።

በተጨማሪም ምርመራ ጨርሰው ወደ ሌላ ክፍል ሲዘዋወሩ ለ42 ቀናት ከአልጋ ጋር ለ24 ሰዓት በካቴና በማሰር፣ 37 የሚሆኑ ተበዳዮች ፍርድ ቤት ረበሻችሁ በማለት ከ3 እስከ 6 ወር እጃቸውን በካቴና አስሮ ጨለማ ቤት ውስጥ በማሰር፣ ግለሰቦች የለበሱትን ልብስ በማስወለቅ በቲሸርትና በቁምጣ በማስለበስ እና በፌሮ ብረት እንዲደበደቡ በማድረግ ኢ- ሰብአዊ ድርጊት እንዲፈጸምባቸውም አድርገዋል ተብሏል።

እናም  በፈጸሙት ስልጣንን ያለአግባብ የመጠቀም ወንጀል መከሰሳቸው ነው የተነገረው።

የተከሳሽ ጠበቆች የዋስትና መብታቸው እንዲከበር የተከራከሩ ቢሆንም የተከሰሱበት ወንጀል የዋስትና መብት የሚያስከለክል በመሆኑ ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም።

ተከሳሾችም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት ዐቃቤ ህግ የመሰረተባቸው ክስ በችሎቱ ተነቦ ለቀረበባቸው ክስ መልስ ይዘው ለመቅረብ ለየካቲት 27/ 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መያዙን ከፌደራል ከጠቅላይ አቃቤ ህግ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።