ሚያዚያ ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአዲስአበባ በሾላ እና በሳሪስ ገበያዎች የሸቀጦች ዋጋ መጠነኛ መረጋጋት ቢታይባቸውም ከሕዝቡ የመግዛት አቅም ጋር ሲነጻጸር አሁንም ዋጋቸው ውድ መሆኑን ዘጋቢያችን ያነጋገርናቸው ሸማቾች ገልጸዋል፡፡
በገበያዎቹ ተዘዋውሮ የተመለከተው ዘጋቢያችን የፈረንጅ ሽንኩርት በኪሎ ከ12- 14 ብር፣ የአበሻ ሽንኩርት ከ20-26 ብር፣ ነጭ ሽንኩርት ከ40-45 ብር በመሸጥ ላይ መሆናቸውን ገልጿል።
ቅቤ ለጋ የሚባለው በኪሎ ከ170-190 ፣ መካከለኛ ከ170-180፣ በሳል ከ155-170 ብር እየተሸጠ ሲሆን አንድ ዕንቁላል የአበሻ ከ2 ብር ከ70 ሳንቲም አስከ 2 ብር ከ75 ሳንቲም፣ የፈረንጅ ዕንቁላል ከ2 ብር ከ75 እስከ 2 ብር ከ80 ሳንቲም ፣ በመሸጥ ላይ ነው፡፡
የአበሻ ዶሮ ከብር 120 እስከ 180 የሚሸጥ ሲሆን የፈረንጅ ዶሮ ከ100 እስከ 120 ብር ይገኛል፡፡ ታርዶ የተዘጋጀ የአበሻ ዶሮ በየሱፐርማርኬቱ ከ80 እስከ 100 ብር የሚሸጥ ሲሆን፣ የፈረንጅ ዶሮ በኪሎ ከ70-80 ብር ገደማ ይሸጣል፡፡ የበግ ገበያ ሙክት የሚባለው ከ2 ሺ ብር በላይ የሚጠየቅበት ሲሆን መካከለኛ በግ ከ1200 እስከ 1500 ብር ፣ጠቦት ከ750 እስከ 1200 ብር እየተጠየቀበት ይገኛል፡፡ የሠንጋ ዋጋ የደለበው ከ10 ሺህ እስከ 15 ሺህ ብር እየተጠየቀበት መሆኑን ገልጿል።
በበዓሉ ገበያ የቀይ ሽንኩርት ዋጋ ትንሽ ጭማሪ ከማሳየቱ በስተቀር ሌሎች ሸቀጦች የመረጋጋት ሁኔታ ማሳየታቸውን አንዳንድ ያነጋገርናቸው ሽማቾች የገለጹ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በገበያዎቹ ያለው ሸቀጦች ዋጋም የተረጋጋ ቢመስልም ግን ከሕዝቡ የመግዛት አቅም አንጻር ሲታይ አሁንም ውድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡