በጃቢጠህናን ከአምስት ሺህ በላይ ነዋሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ

ሚያዚያ ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በምእራብ ጎጃም ዞን በጃቢጠህናን ወረዳ የሆዳንሽ ቅዱስ ገብርኤል ቀበሌ ኗሪዎች የሆኑ ከአምስት ሺህ በላይ ነዋሪዎች ህገ-ወጥ ግንባታ በሚል ቤታቸው እንዲፈርስ የወጣውን ትዛዝ በመቀዋወም አደባባይ ወጥተዋል፡፡

የተቃውሞ ሰልፉ የተደረገው የወረዳው ከፍተኛ ባለስልጣናት ሚያዝያ 5 ፣ 2006ዓ.ም የቀበሌውን ህዝብ ሠብሰብው ከ808 በላይ ህገወጥ ቤቶች ይፈርሳሉ በማለት ያደረጉትን ንግግር ተከትሎ ነው።

” የመኖሪያ ቤት ጥያቄ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ነው” ያሉት ሠልፈኞቹ፣  ተቸግረን የገነባነውን ቤት በመንግስት ትዕዛዝ እንደዋዛ ሊፈርስ አይገባም ብለዋል፡፡

“መንግስት መመሪያውን በወቅቱ ባለማውጣቱና የወጣውን መመሪያ ተግባራዊ ባለማድረጉ በፈጠረው ስህተት ቤቶቻችሁ ሁሉ ይፈርሳሉ የሚል ትዛዝ ለምን አስተላለፈ?በበርሃ አረን፣  ከስለንና የደም እዳ ከፍለን የገነባነውን መኖሪያ ቤታችን ከላያችን ላይ ሲፈርስ መንግስት ለእኛ ለዜጎቹ ምን አማራጭ ይዞልን ነው? ልጆቻችንስ የት እናድርሳቸው? ሁሌ ተፈናቃዮችና ስደተኞች ከሆንን በነፃነት ቤት ሠርተን የምንኖርበት ሀገር ወዴት ነው? ህግ ወደ ኋላ ዞሮ በእኛ ላይ ተግባራዊ እንዲደረግ የተፈለገውስ ከምን አንፃር ነው? ” የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችን ያነሱት ሠልፈኞቹ፣  ከዞንና ከወረዳ ባለስልጣናቱ ጋር ሳይግባቡ ተለያይተዋል፡፡

ህገወጥ ሠላማዊ ሠልፍ በማድረግ ሽብርና ሁከት ፈጥራችኋል በሚል በዞንና ወረዳ ባለስልጣናት ዛቻና የማስፈራራት ምላሽ ያልተደናገጡት ሠልፈኞቹ ፣ ጉዳዩ በህጋዊ መንገድ ትክክለኛ መፍትሄ እስከሚያገኝ እንታገላለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በሌላ ዜና ደግሞ በህገወጥ የጦር መሳሪያ ሠበብ መንግስት የሚያደርገው አሰሳ ደህንነታችንን አደጋ ላይ ጥሎታል ሲሉ የአማራ ክልል አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡

የኢህአዴግ መንግስት አማራ ክልል ላይ ባደረገው ተደጋጋሚ የጦር መሳሪያ ገፈፋ አርሶ አደሩ ባዶ እጁን መቅረቱን ጠንቅቆ እያወቀ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ገፈፋ በሚል ዳግም ህዝብን ለምን እንደሚያንገላታ አልገባንም ያሉት አርሶ አደሮቹ ፣ በዚህ የመንግስት እንቅስቃሴ የተረጋጋ ህይወት መምራት አልቻልንም በማለት ተናግረዋል፡፡

የቋሪትና ጃቢጠህናን ወረዳ አርሶ አደሮች ህገወጥ የጦር መሳሪያ ገፈፋ በሚል ዘመቻ በተደጋጋሚ ሰለባ እንደሆኑና በደህንነት ስጋት ላይ መሆናቸውን ተናግረው ፣ አሁንም የመጀመሪያዎቹ ሰለባዎች እኛ ሆነናል ሲሉ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ቀብራችሁ ደብቃችኋል በሚል ቤታቸው የተቆፈረባቸው አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡

ቀጣዩን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ የአማራ ክልል አርሶ አደሮች ያምፃሉ በሚል ስጋት በሶስት ዙር የጦር መሳሪያ ገፈፋ ሊካሄድ እቅድ እንደተያዘ ከኢህአዴግ ደህንነት አካላት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

መሳሪያ ደብቃችሁዋል በሚል ሰበብ በአርሶ አደሮች ላይ ኢ-ስብዓዊ የሆነ ደብደባና ግርፋት መፈፀሙን አርሶ አደሮች ለክልሉ ዘጋቢያችን ነግረዋታል።