የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት ከስልጣን የምነሳ ከሆነ ክልሉ የራሱን እድል በራሱ ይወስናል አሉ

ሚያዚያ ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢህአዴግ ምክር ቤት በሶማሊ ክልል የሚፈጸመው ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት በክልሉ ያሉትን ባለስልጣኖች ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የኢህአዴግን ባለስልጣኖችን በአለማቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት የሚያስጠይቅ መሆኑን ድምዳሜ ላይ የደረሰው ኢህአዴግ፣  ፕሬዚዳንት አብዲ ሞሃመድ ኡመርን ለማውረድ እንቅስቃሴ መጀመሩ  ፕሬዚዳንቱ ይህንን ንግግር እንዲናገሩ እንዳደረጋቸው ምንጮች ገልጸዋል።

አቶ አብዲ   የእርሳቸው ታማኝ ደጋፊ የሆኑ በውጭ አገራት የሚኖሩ የክልሉን ተወላጆች ጅጅጋ ውስጥ በሰበሰቡበት ወቅት ፣ እርሳቸው ከስልጣን የሚወርዱ ከሆነ፣ ክልሉ የእራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከመገንጠል የሚለውን የህገመንግስት አንቀጽ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ዝተዋል። ኢህአዴግ አንዳንድ እጃቸውን ከሰጡና በሃይል ታፍነው ከተወሰዱ የቀድሞ የኦብነግ አመራሮች ጋር የጀመረው ቅርርብ አቶ አብዲን አላስደሰተም።

አቶ አብዲ በእርሳቸውና በተወሰኑ የህወሃት ጄኔራሎች የሚመራ   ልዩ ሚሊሺያ የሚባል ሰራዊት  መቋቋማቸው ይታወቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ታላቁዋን ሶማሊያን ለመመስረት አላማ ይዞ ሲንቀሳቀስ ለነበረው ሙሀመድ አብዱላህ ሃሰን በጅጅጋ ከተማ የተሰራው ሃውልት ተመርቋል። በቅኝ ግዛት ዘመን ለታላቁዋ ሶማሊያ መመስረት ሲታገል የነበረው ሙሀመድ ሃሰን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ተከታታይ ጦርነት አድርጎ ነበር።

የክልሉ መንግስት የኢትዮጵያን አንድነት የማይፈልገውንና ለታላቁዋ ሶማሊያ መመስረት ሲታገል ለነበረው ሰው ሃውልት ማቆሙ ብዙዎችን ያስገረመ ክስተት ሆኗል። ሙሃመድ ሃሳን በሞቃዲሾ ከተማም  እንዲሁ ታላቅ ሃውልት ተገንብቶለታል።