ሰማያዊ ፓርቲ ታላቅ ህዝባዊ ተቃውሞ ማዘጋጀቱን አስታወቀ

ሚያዚያ ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ፓርቲው ” ሰላማዊ ትግላችንን አጠናክረን በመቀጠል የተነጠቁ መብቶቻችንን እናስመልሳለን፡” በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ ” ሰማያዊ ፓርቲ በመንግስት የሚፈጽሙ ሕገ ወጥ ድርጊቶች የሠብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆሙ ለመንግስት አካላት በተደጋጋሚ ጊዜያት ጥሪ ቢያቀርብም የሚሰማው ማጣቱን ገልጿል።

በአገሪቱ የሚታዩ ችግሮች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ለማድረግ  እሁድ ሚያዚያ 19/2006 ዓ.ም ከጠዋቱ 4 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት የሚቆይ ከፓርቲ ጽ/ቤት እስከ ጃን ሜዳ የሚደርስ ታላቅ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ ማዘጋጀቱን ፓርቲው በመግለጫው ጠቅሷል። የሠላማዊ ሰልፉን ቀንና ሰዓትም በአዋጅ ቁጥር 031983 መሠረት ለሚመለከተው አካል በደብዳቤ ማሳወቁንም ገልጿል።

በታላቁ ሕዝባዊ ሰልፍ ላይ መንግስት በእምነት ጣልቃ ገብነቱን እንዲያቆም፣ ዜጎችን ከቀያቸው ማፈናቀሉ እንዲቆምና የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ” የሚሉ ጥያቄዎች እንደሚነሱ የገለጸው ፓርቲው ፣ “ለገዢው ፓርቲ ስልጣን እንጅ ለህዝብ የማይጨነቁት ተቋማት በተለይ የውሃ፣ የመብራት፣ የቴሌ ኮሚኒኬሽንና የትራንስፖርት አገልግሎቶች ሕዝብን እያመማረሩ በመሆናቸው በሠላማዊ ሠልፉ ላይ የሚነሱ ወሳኝ ጥያቄዎች ይሆናሉ” ብሎአል።

የተነጠቁ መብቶቻችንን እናስመልስ ዘንድ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ሲቪክ ማህበራትና ሚዲያው ከሚደረገው ጥረት ጎን መቆም ሀገራዊ ግዴታ እንዲወጡ ፓርቲው ጥሪውን አስተላልፎአል።