በምርጥ ዘር ጥራት መጓደል ምክንያት ከፍተኛ ሃብት እየባከነ ነው ተባለ

ሚያዚያ ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ ምርጥ ዘር ድርጅት እንዳስታወቀው ባለፉት አመታት ለአርሶደሩ የቀረቡ የምርጥ ዘር ማሻሻያ ዝርያዎች የመብቀልና ምርት የማፍራት ችግር ገጥሞአቸዋል። በዚህም የተነሳ በየአመቱ ከ150 ሺ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለብክነት እየተዳረገ ነው። በዚህ አመት ብቻ 25 ሺ 97 ኩንታል ምርት ዘር ባክኖ መቅረቱን ድርጅቱ አስታውቋል።

በየዓመቱ ጥራታቸውን ያልጠበቁ ዝርያዎች ያለአግባብ እየቀረቡ ከ2ዐሽ ሄከታር በላይ መሬት ተገልብጦ እንደገና እንደሚዘራ የገለጸው ድርጅቱ፣  በዚህ ዘር ምክንያት በሰፊው እየተጠቃ ያለው የአማራ፣ የደቡብ እና የኦሮምያ ክልል  አርሶደሮች ናቸው፡፡

አርሶ አደሩ ምርት ዘር በውድ ዋጋ ገዝቶ በእጥፍ ምርት ሲጠብቅ አብዛኞቹ የታቀደውን ያህል ምርት ሳይሰጡ በምርጥ ዘር የምርምር ደረጃ መክነው ይቀራሉ። አርሶ አደሩ “ለምን?’ የሚል ጥያቄ ሲያቀርብም የሚሰጠው መልስ ከዝናብ ቀድሞ መግባት ወይም መዘግየት ጋር የተያያዘ ነው።

በመልካም አሰተዳደር ኮማንድ ፖስት የተደረገ ይፋ ያልሆነ ጥናት እንደሚያሳየው እስካሁን በአጠቃላይ  1 ቢሊዮን 6 መቶ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ምርጥ ዘር  ለብክነት ተዳርጓል። አርሶአደሮች መንግስት  በምር  ዘር፣ በማዳበሪያና በግብር እዳ እያስጨነቃቸው እንደሚገን በተደጋጋሚ ይገልጻሉ።