መስከረም ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የሳዑዲዓረቢያ መንግስት ኢትዮጵያን ከሐጂና ዑምራ ጉዞ በድንገት ማገዱ ሙስሊሙን ኀብረተሰብ ማስደንገጡን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች አረጋገጡ፡፡
በየዓመቱ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ለሐጂ ጸሎት ወደ ሳዑዲዓረቢያ የሚያደርጉት ሃይማኖታዊ ጉዞ የአረፋ በዓል ሊደርስ አንድ ወር ሲቀረው ጀምሮ የሚከናወን መሆኑን አስታውሰው ዘንድሮም በሙስሊሙ ኀብረተሰብ አመኔታ ያጣው የኢትዮጵያ እስልምና ም/ቤት(መጅሊስ) ጉዞውን እንደሚያስተባብር ማስታወቂያ በይፋ አስነግሮ የነበረ ቢሆንም የሳዑዲ መንግስት ግን በተለየ ሁኔታ ኢትዮጵያን ከጉዞው ማገዱን አስታውቋል፡፡
የሳዑዲ መንግስት ለምን ይህን እርምጃ እንደወሰደ በይፋ የገለጸው ነገር ስለመኖሩ እንደማያውቅ የጠቀሰው ምንጫችን እየተነገረ ያለው ምክንያት ግን ከሙስሊሙ ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ በመጅሊሱ ወይም በእስልምና ምክር ቤቱ ላይ እምነት በማጣቱ ሳይሆን እንደማይቀር ጠቅሰዋል፡፡
ጉዞውን አስተባብራለሁ በሚል ከሙስሊሙ ኀብረተሰብ ገንዘብ እየሰበሰበ የነበረው መጅሊስ የጉዞው እገዳ ከተሰማ በኃላ ገንዘባችንን መልስ በሚል ጥያቄዎች መወጠሩ ታውቋል፡፡
እንደምንጫችን ዘገባ በሐጂና ዑምራ ጉዞ በየዓመቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን በነፍስወከፍ እስከ40ሺ ብር በመክፈል እንደሚጓዙ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ከሳውዲ አረብያ መንግስት ኢምባሲ ተወካይ ጋር በጋራ ይሰራሉ ያላቸውን የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩን የአቶ ጁነዲን ሳዶን ባለቤት ማሰሩን በይፋ አስታውቆ ነበር። ሚኒስትር ጁነዲን ሳዶም ለመገናኛ ብዙሀን በበተኑት ወረቀት ባለቤታቸው ከሳውዲ አረብያ ኢምባሲ ጋር ያላቸው ግንኙነት እናታቸውን ከመሞታቸው በፊት በአርሲ የሚገኝን መስጊድ እንዲያሰሩ አደራ ብለዋቸው ስለነበር፣ በዚያ መሰረት ከሳውዲ ኢምባሲ ያገኙትን እርዳታ ለመቀበል ባለቤታቸው ወደ ኢምባሲ እንደተመላለሱ እንጅ የሙስሊሞችን ተቃውሞ በመደገፍ አለመሆኑን ገልጠዋል።
መንግስት የሙስሊሞችን ተቃውሞ ለማቀጣጠል ገብተዋል ያላቸውን ሶስት የሳውዲ አረብያ ዜጎችን ከአገር ማባረሩም ይታወሳል።
የመንግስትን እርምጃ ተከትሎ ይመስላል ሳውዲ አረብያ ፣ የመንግስት ደጋፊ በሆነው መጅሊስ አስተባባሪነት የሚካሄደውን የሀጂና ኡመር ጉዞ ለመሰረዝ የወሰነው።
የሳውዲ አረብያ መንግስት የወሰደው እርምጃ ምናልባትም በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት እየሻከረ መምጣቱን የሚያመላክት ነው ይላሉ የፖለቲካ ተንታኞች። ሳውዲ አረብያ በቱጃሩ በሼክ ሙሀመድ ሁሴን አማካኝነት በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ አፍስሳለች።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መሪዎቻቸው ታስረውም እንኳ ተቃውሞአቸውን አላቆሙም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ህዝብ በሚውልባቸው ቦታዎች የሀይማኖት መዝሙሮች እንዳይሰሙ እንዲሁም የሀይማኖት ጥቅሶች እንዳይለጠፉ የሚከለከል አዋጅ ሊያወጣ ነው።
በታክሲዎች፣ ሆቴሎችና መናፈሻ ቦታዎች የሀይማኖት መዝሙሮች አይደመጡም። እንዲሁም በመንገዶች ላይ የሚደረጉ ሀይማኖታዊ ስብከቶች ይታገዳሉ።
መንግስት ይህን እርምጃ ለመውሰድ የተነሳሳው በአገሪቱ ውስጥ እየታየ የመጣው የሀይማኖት አክራሪነት ስጋት ላይ ስለጣለው መሆኑ ታውቋል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide