በእስር ላይ የሚገኘው የአንድነት ፓርቲ አመራር አቶ አንዱአለም አራጌ ለነጻነት የሚደረገው ትግል እንዲቀጥል አሳሰበ

መስከረም ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በግፍ እስር ላይ የሚገኘው የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ሀላፊው ወጣቱ ፖለቲከኛ አንዱአለም አራጌ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች መስከረም 17 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም በሽብርተኝነት ስም ታስሮ የሚገኘውንና እና የፓርቲው ከፍተኛ አመራር የሆነውን አቶ አንዱዓለም አራጌን በቃሊቲ በመገኘት ጎብኝተዋቸዋል።  አመራሩ የአንድነት ፓርቲ የብሔራዊ ም/ቤት አባል የሆነውንና ቂሊንጦ ታስሮ የሚገኘውን አቶ ናትናኤል መኮንንም ጎብኝተዋል።

አቶ አንዱዓለም ‹‹ትግሉን አጠናክሮ ከመቀጠል ውጭ ምርጫ እንደሌለና የተበታተኑ ተቃዋሚዎች በመሰባሰብ ጠንካራ ኃይል ቢፈጥሩ እንደሚጠቅም ተናግሮ የእሱም አላማ ለሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን መፍጠር እንጅ ሌላ እንዳልሆነ ገልጿል፡፡››

አመራሩም ምንጊዜም ከጎኑ እንደሆኑና ትግሉንም ግቡን እስከሚመታ አጠንክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠውለታል፡፡

የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የእስር ቤቱ ሃላፊዎች አጉላልተዋቸው እንደነበር ጠቅሰዋል።

አቶ አንዱአለም የመንፈስ ጥንካሬው አሁንም እንዳለ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ነጋሶ ፣ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በማንሳትም ተነጋግረው እንደነበር ጠቅሰዋል

አቶ አንዱአለምም ሆነ አቶ ናትናኤል ይግባኝ ለመጠየቅ ፍላጎት የሌላቸው ቢሆንም ፣ ፓርቲያቸው ይግባኝ እንዲጠይቁ በመምከሩ ይግባኝ ለመጠየቅ ማሰባቸውን ተናግረዋል።

አቶ መለስ ዜናዊ ከሞቱ በሁዋላ፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ሀይለማርያም ደሳለኝ የፖለቲካ መሪዎችን የሚፈቱ ይመስልዎታል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ዶ/ር ነጋሶ ” አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የአቶ መለስን ፖሊሲ አስፈጽማለሁ በማለት በይፋ መናገራቸውን አውስተው ፣ በሂደት መልስ ብንሰጥ ይሻላል ብለዋል

አቶ መለስ ዜናዊ በህይወት በነበሩበት ጊዜ የሽብር ጥቃት ለመፈጸመም አሲረዋል ያሉዋቸውን በርካታ የፖለቲካ መሪዎችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ፣ በእስር እንዲቀጡ ማስደረጋቸው ይታወሳል። የከፍተኛው ፍርድ ቤት ሀምሌ 6 ቀን 2004 ዓም በሰጠው የግፍ ፍርድ አቶ አንዱአለም አራጌ፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ እና አቶ ፋሲል የኔአለም በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት አቶ ናትናኤል መኮንን፣ አቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ውቤ ሮቤ እና አቶ ኢቦንግ ሜቶ እያንዳንዳቸው በ18 አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑ ይታወሳል።

እንዲሁም አቶ የሽዋስ ይሁን አለም፣ አቶ ዘለሌ ጸጋስላሴ፣ አቶ አበበ በለው እና አቶ አበበ ገላው እያንዳንዳቸው በ15 አመት ጽኑ እስራት ፣አቶ ምትኩ ዳምጤ እና አቶ መስፍን አማን ደግሞ እያንዳንዳቸው በ14 አመት ጽኑ እስራት ሲቀጡ አቶ ዮሃንስ ተረፈ በ13 አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑ ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide