(ኢሳት ዲሲ–ጥር 29/2011)የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ የሲጋራ ማጨሻ ስፍራን የሚገድብና አልኮልን በብሮድካስት ሚድያ ማስተዋወቅ የሚከለክለውን አዋጅ አፀደቀ።
ከ21 ዓመት በታች ለሆኑ ታዳጊዎች አልኮል መሸጥ ክልክል መሆኑም ተገልጿል።
የምክር ቤቱ አባላትም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያዩ በኋላም አፅድቀውታል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ዛሬ ያፀደቀው የሲጋራ ማጨሻ ስፍራን የሚገድበውና አልኮልን በብሮድካስት ሚድያ ማስተዋወቅ የሚከለክለውን አዋጅ በመስሪያ ቤቶች፣ በጤና ተቋማት እና የወጣቶች መዝናኛ በሚገኙባቸው አካባቢዎች በ100 ሜትር ርቀት ውስጥ ሲጋራ ማጨስ ክልል መሆኑን ይደነግጋል።
ማንኛውንም የአልኮል ምርት በብሮድካስት ሚዲያ ማስተዋወቅ እንደማይቻልም አዋጁ አስቀምጧ።
ከአልኮል መጠጦች ጋር በተያየዘም ከ21 ዓመት በታች ለሆኑ ታዳጊዎች አልኮል መሸጥ ክልክል መሆኑም ተገልጿል።
በኢትዮጵያ የጫትና የሺሻ ሱስ በወጣቶችና በመላው ሕብረተሰብ ዘንድ ከፍተኛ የሀገር ቀውስ እያስከተለ ቢሆንም ይሕንኑ የተመለከተ ሕግ ግን አለመውጣቱ ታውቋል።
ጫት በመንግስት በኩል ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ተደርጎ ስለሚወሰድ ቁጥጥር ለማድረግ ፍላጎት እንደሌለ ሲገለጽ ቆይቷል።
በትግራይ ክልል ብቻ ጫት መሸጥም ሆነ መጠቀም በህግ ክልክል ተደርጎ የቆየ ቢሆንም በአፈጻጸሙና በቁጥጥሩ ላይ ግን ችግር አጋጥሞ መቆየቱ ይታወሳል።
የአማራ ክልላዊ መንግስትም ጫትን መጠቀም የሚከለክ ሕግ አውጥቻለሁ ቢልም እስካሁን በተግባር እንዳልዋለ ምንጮች ይናገራሉ።