ወርቅና ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ሐገር ገንዘብ በኢትዮጵያ ድንበር ተያዘ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 29/2011)በሕገወጥ መንገድ ከሃገር ሊወጣ የነበረ 7 ኪሎግራም ወርቅና ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ሐገር ገንዘብ ትላንት በኢትዮጵያ ድንበር ላይ መያዙ ተገለጸ።

በሕገወጥ መንገድ ከሐገር ሊወጣ ሲል በቶጎ ውጫሌ ኬላ ላይ ከተያዘው 7ኪሎ ግራም ወርቅ በተጨማሪ 1 ሚሊየን 527ሺ 14 የአሜሪካን ዶላር እንዲሁም 8ሺ 280 ዩሮና 31ሺ 900 ፓውንድ መያዙም ተመልክቷል፡

የገቢዎች ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በተጨማሪም 25ሺ 665 የካናዳ እንዲሁም 8 ሺ 880 የአውስትራሊያ ዶላርን ጨምሮ የተለያዩ ሐገራት ገንዘቦች ከነግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር ውሏል።

ካሚል ኡመር መሃመድ፣መሐሪ ካሪም፣መሃዲ ኡመር ኢብራሒምና ካሊድ አብደላ አሊ ከወርቁና ከገንዘቡ ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል።

ወርቅና ገንዘቡን እንዲሁም ግለሰቦቹን ይዞ መኪናውን ሲያሽከረክር የነበረው ግለሰብ በማምለጡ እየተፈለገ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች አበቤ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።