የፖለቲካ ፓርቲዎች ህገ መንግስቱን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ ይደነገጋል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 29/2011)የፖለቲካ ፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነድ ፓርቲዎች ህገ መንግስቱን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ፣ ህገ መንግስቱን ከሚፃረሩ ድርጊቶች እንዲታቀቡም ይደነግጋል ተባለ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ግንኙነታቸውንና የተናጠል እንቅስቃሴያቸውን  የሚገዛ የአሰራር ስርዓት ረቂቅ ቃል ኪዳን ሰነድ ላይ ተወያይተዋል።

በውይይቱ የክልልና የሃገር አቀፍ ፓርቲዎችን ጨምሮ በቅርቡ ከውጭ ሀገር የተመለሱ በምዝገባ ሂደት ላይ የሚገኙ በጥቅሉ 103 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተገኝተዋል።

በጋራ ምክር ቤቱ የቀረበው የቃልኪዳን ሰነድ በሦስት ምዕራፎችና በ20 አንቀጾች የተከፈለ ነው።

የቃል ኪዳን ሰነዱ ፓርቲዎች ህገ መንግስቱን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ፣ ህገ መንግስቱን ከሚፃረሩ ድርጊቶች እንዲታቀቡም ይደነግጋል ተብሏል።

ሃይልን መጠቀም የመንግስት ብቻ መሆኑ እና ለዚህ መርህም ሁሉም ፓርቲዎች ተገዢ እንዲሆኑ በሰነዱ ተደንግጓል።

ማንኛውም የፓርቲ አመራር አባል ወይም ደጋፊ በምንም ሁኔታ ህግን የማስፈፀም ተግባር ውስጥ መግባት እንደማይችልም ተደንግጓል።

በፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ በደጋፊዎቻቸው ባለቤትነት የሚተዳደሩ የማህበራዊ ድረ ገፆች እና የህትመት ውጤቶች ማህበራዊ ጥላቻን፣ መቃቃርን፣ አመፅን፣ የመለያየትን እና ህገ ወጥ ድርጊቶችን የማደፍረስ ውጤት ያላቸው መልዕክቶችን ከማስተናገድ እንዲቆጠቡ የማድረግ ሃላፊነት አለባቸው።

ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የማህበራዊ ትስስር ገጻቸውን በይፋ ለህዝብ ማሳወቅ አለባቸውም ተብሏል።

በሰነዱ እንደተመለከተው ማንኛውንም የመንግስት ሀብት፣ ገንዘብ፣ የሰው ሃይል፣ ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ንብረት ለፖለቲካ ስራ ጥቅም ላይ አይውልም ።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በቃል ኪዳን ሰነዱ ላይ የተቀመጡ ህግጋትን ከጣሱ ጥፋታቸውን እንዲያርሙ ይነገራቸዋል ሆኖም ከጥፋታቸው የማይታረሙ ከሆነ የጋራ ምክር ቤቱ ርምጃ እንደሚወስድ ሰነዱ ይደነግጋል ነው የተባለው።

ህጉን በማርቀቅ ውስጥ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ለተነሱ ጥያቄዎቹ ምላሽ ሰጥተዋል።

የአሁኑ ረቂቅ ደንብ አዋጅም አይደለም ሲሉ ወይዘሪት ብርቱካን ገልጸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸው ተስማምተው የሚመሩበት ቃልኪዳን መሆኑን በመግለጽ የከዚህ ቀደሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የስነ ምግባር ደንብን አይመለከትም ብለዋል።