የሱዳኑ መሪ የፖለቲካ ድርጅቶች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ፈቀዱ

ሚያዚያ ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ፕሬዚዳንቱ ትናንት ባካሄዱት ፕሬዚዳንታዊ አዋጅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስራቸውን በነጻነት እንዲሰሩና እንዲሰበሰቡ እንዲሁም የመንግስትን ሚዲያ እኩል እንዲጠቀሙ ፈቅደዋል።

ውሳኔው በአገሪቱ ውስጥ የፖለቲካ ውይይት ለማድረግ አዲስ ጅማሮ ነው ተብሎለታል። ፕሬዚዳንት በሽር 83 ከሚሆኑ የአገሪቱ የፖለቲካ ድርጅትቶች ጋር በመጪው እሁድ ውይይት ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል።

ፕሬዚዳንቱ የፕሬስ ነጻነት ያለምንም ገደብ እንዲከበር እንደሚያደርጉም ቃል ገብተዋል። ፕሬዚዳንቱ መንግስትን በሃይል ለማውረድ የሚታገሉ ሃይሎች በስብሰባው ተሳትፈው ያለምንም ችግር ወደ ጫካ እንዲመለሱ እንደሚፈቅዱ መናገራቸው ብዙዎችን አስገርሟል።

የፕሬዚዳንቱን ንግግር ተከትሎ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች  በርካታ የተቃዋሚ አባላትን ከእስር ለቀዋል። እስካሁን ድረስ ምን ያክል የተቃዋሚ ፓርቲዎች የፕሬዚዳንቱን ጥሪ ተቀብለው አወንታዊ መልስ እንደሰጡ አልታወቀም።