የሰብአዊ መብት ረገጣ የፈጸሙ ግለሰቦች ለፍርድ አልቀረቡም ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 15/2010) በኢትዮጵያ በአገዛዙ ታጣቂዎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ረገጣዎችና ወንጀሎች ተጣርተው ፈጻሚዎቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንዳልተደረገ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሪፖርት አመለከተ።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2017 ሪፖርት ኢትዮጵያን አስመልክቶ ባሰፈረው የሰብአዊ መብት አያያዝ በሃገሪቱ ተጠያቂነት ባለመኖሩ በርካታ የሰብአዊ ጥሰቶች በመፈጸም ላይ ናቸው።

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተወሰዱ የማሻሻያ ርምጃዎች አዎንታዊ ለውጥ መታየቱንም ሪፖርቱ አመልክቷል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ የሰብአዊ መብት አያያዝ ሪፖርት የየሃገራቱን ሁኔታ በመዳሰስ በየአመቱ መግለጫ የሚሰጥበት አሰራር ነው።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በየአመቱ የሚወጣው ይህ ሪፖርት የሰብአዊ መብት ረገጣዎችን በመዘርዘር ማስተካከያ እንዲደረግ ጥሪ ያቀርባል።

ይህ ሪፖርት አሜሪካ በተለያዩ ሀገራት የምትከተለው ፖሊሲ እንደ መነሻ መረጃ እንደሚያገለግልም ይነገራል።

እናም የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የ2017 የሃገራት የሰብአዊ መብት አያያዝ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል።

ኢትዮጵያን በተመለከተ ባወጣው ሪፖርትም በሀገሪቱ በርካታ ግድያዎች፣እስርና ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ረገጣ እንደሚፈጸም ነው የዘረዘረው።

ይህም ሆኖ ደግሞ በኢትዮጵያ የሕግ ተጠያቂነት የለም ብሏል ሪፖርቱ።

በኢትዮጵያ የአገዛዙ ታጣቂዎች በርካታ ሰዎችን ገድለውና የሰብአዊ መብት ረገጣ ፈጽመው በሕግ የሚጠየቁበት ሁኔታ አለመኖሩን ሪፖርቱ አመልክቷል።

በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ በዚሁም ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸው ተዘርዝሯል።

በአሁኑ ጊዜም በሀገሪቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጎ ተመሳሳይ የሰብአዊ መብት ጥሰት ይፈጸማል ብሏል።

በኢትዮጵያ በ2017 በተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ረገጣዎች የሰው መሰወር፣ጅምላ እስርና ግድያ እንደነበርና የዜጎች መሰረታዊ መብቶችም አለመከበራቸውን ሪፖርቱ ገልጿል።

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተወሰዱ ርምጃዎች እስረኞችን መልቀቅን የመሳሰሉ በጎ ሁኔታዎች ቢኖሩም አሁንም መሰረታዊ ለውጥ እንደሚያስፈልግ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመታዊ የሰብአዊ መብት አያያዝ ሪፖርት አመልክቷል።