ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወልቃይት የአማራ ማንነት ኮሚቴ አባላትን አነጋገሩ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 12/2010)ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወልቃይት የአማራ ማንነት ኮሚቴ አባላትን አነጋገሩ።

የወልቃይት ጉዳይ በህገመንግስቱና በህጉ የሚፈታ ነው ማለታቸውም ተገልጿል።

ዛሬ በጎንደር ጎሃ ሆቴል ከጎንደር ህዝብ ጋር በተደረገ ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመቀሌ ስለወልቃይት የተነሳው ከማንነት ጋር የተያያዘ ጥያቄ አይደለም በማለት መግለጻቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

የሱዳን የድንበር ጉዳይንም በተመለከተ ከሱዳኑ መሪ አልበሽር ጋር እንደሚነጋገሩ አስታውቀዋል።

በእስር ላይ የሚገኙት የአቶ መላኩ ፈንታ ጉዳይም ተነስቶ እየታየ ያለ ጉዳይ በመሆኑ በቅርቡ እናሳውቃችኋለን  ብለዋል።

የወልቃይት የአማራ ማንነት ኮሚቴ አባላት መስራችና ሊቀመንበር የጠቅላይ ሚኒስትሩን አቋም ተስፋ የሚሰጥ ብለውታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በጎንደር ከህዝቡ ጋር ባደረጉት ውይይት በርካታ ጥያቄዎች ተነስተዋል።

በኢትዮጵያና በሱዳን መሀል ያለው የድንበር ችግር መፍትሄ እንዲሰጠው ተጠይቋል።

ባለስልጣናት ፎቅ ቤት መኪና ሌሎች ሃብቶችን ሲያካብቱ የሀብቱ ምንጭ ከየት እንደመጣ መጣራት እንዳለበት ከተሰብሳቢው ተነስቶ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርቧል።

በኢትዮጵያ ብሄራዊ እርቅ እንደሚያስፈልግ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተገለጸ ሲሆን ትኩረት እንዲሰጡበት ተጠይቋል።

የመከላከያ ሰራዊቱ ጉዳይም በተሰብሳቢው ዘንድ ተነስቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያስቡበት ሀሳብ መቅረቡም ተገልጿል። መከላከያ ሰራዊቱ ለአንድ ወገን ያደላ መሆኑ በስብሰባው ተነስቷል።

በእስር ላይ ስለሚገኙት የቀድሞ የገቢዎችና ጉምረክ ባልስልጣን አቶ መላኩ ፈንታም በስብሰባው መነሳቱን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። “እንዴት አንድ ሀገር የሚመራ ባለስልጣን ሚስትህን ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመንግስት መኪና ልከሃል ተብሎ ይህን ያህል ስቃይ ይደርስበታል?” አንድ የስብሰባው ተሳታፊ ስለ አቶ መላኩ ፈንታ ጠይቀዋል።  ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም “እያየነው ያለ ጉዳይ ነው፣ ስንጨርስ እናሳውቃለን” ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የመቀሌው ቆይታ በጎንደሩ ጉብኝታቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በጎንደር ፋሲል ስታዲየም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በሚያደርጉበት ጊዜ የወልቃይት ጉዳይ እየተነሳ ተቃውሞ ሲሰማ እንደነበረ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግራቸውን ሳይጨርሱ በስታዲየም የነበረው ህዝብ  አቋርጦ መውጣት መጀመሩንም የአይን እማኞች ተናግረዋል።

በስታዲየሙ ስነስርዓት በህወሀት የተደራጁና የቅማንትን የመብት ጥያቄ የሚያነሱ ግለሰቦች የተለያዩ መፈክሮችን ይዘው መገኘታቸውም ታውቋል።

ህወሀት በቅማንት ስም ያደራጃቸውን ግለሰቦች በማሰልጠን ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከወልቃይት ይልቅ የቅማንትን ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጡበት በዝግጅት ላይ እንደነበረ ኢሳት በትላንቱ ዜና እወጃው መዘገቡ የሚታወስ ነው።

ከቀትር በኋላ በጎሀ ሆቴል በተደረገ ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በወልቃይት ጉዳይ ላይ በመቀሌ ከያዙት አቋም የተለየ አስተያየት ሰጥተዋል።

የወልቃይት ጉዳይ የሚፈታው በህገመንግስቱና በህግ ብቻ ነው ማለታቸው መቀሌ ላይ ከተናገሩት በተቃራኒው የሚወሰድ እንደሆነ ታዛቢዎች ገልጸዋል። በመቀሌ ስለወልቃይት የተናገሩት የአማራን ህዝብ በጣም እንዳሳዘነ በግልፅ ከተሰብሳቢዎች ቀርቧል።

በቅርቡ ከእስር የተፈቱት የወልቃይት የአማራ ማንነት ኮሚቴ አባላት ባለፉት አርባ ዓመታት በወልቃይት ተወላጆች ላይ የደረሰውን ግፍ በዝርዝር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

‘’ወንድ ልጅ ራሱን ይዞ ያለቀሰበት ጊዜ ቢኖር እርስዎ መቀሌ ላይ በወልቃይት ጉዳይ ከተናገሩ በኋላ ነው። ወልቃይት ብዙ ስቃይ ይፈፀማል። በአማርኛችን እንኳ መዝፈን አንችልም። አስከሬን በወጉ መቅበር አንችልም። አሁንም በወልቃይት ጉዳይ እስር ቤት የሚገኙ አሉ።’’ በማለት ከኮሚቴ አባላት አንዱ የሆኑት አቶ አታላይ ዛፌ ተናግረዋል።

ዶክተር አብይም እኔ መቀሌ ላይ ስለ ወልቃይት ጥያቄ አልቀረበልኝም የተናገርሁት በዚህ አግባብ አይደለም።

ማንም የአማራ ህዝብ በዚህ እንዲቀየም አልፈልግም። በግል ኮሚቴውን ማውያየት እፈልጋለሁ በማለት የመለሱ ሲሆን ለስሰባው  ቅርበት ያላቸው ወገኒች ዘግበዋል።

የኮሚቴው አባላትን ለብቻ ማነጋገራቸውም ታውቋል። ጉዳዩን የተከታተሉት የወልቃይት የአማራ ማንነት ኮሚቴ መስራችና ሊቀመንበር አቶ በሪሁን ጥሩ ለኢሳት እንደናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በወልቃይት ጉዳይ የተናገሩት መልካም ጅምር ነው።

ኮሚቴው ከሽብርተኝነት ፍረጃ ወጥቶ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እውቅና አግኝቶ መወያየታቸን ተስፋ ይሰጣል ብለዋል- አቶ በሪሁን።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የጎንደር ቆያትቸውን አብቅተው ለጣና ፎረም ስብሰባ ላይ ለመገኘት ባህርዳር መግባታቸውም ታውቋል።