ዶናልድ ያማማቶ በኢትዮጵያ፣ኤርትራና ጅቡቲ የሚያደርጉትን ጉዞ ጀመሩ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 15/2010) በአሜሪካ ወጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ተጠባባቂ ረዳት ሚኒስትር ሚስተር ዶናልድ ያማማቶ በኢትዮጵያ፣ኤርትራና ጅቡቲ የሚያደርጉትን ጉዞ ጀመሩ።

እሁድ ኤርትራ ርዕሰ መዲና አስመራ የገቡት ዶናልድ ያማማቶ ከዚያም ወደ ጅቡቲ አቅንተው አዲስ አበባ ላይ ተልዕኳቸውን እንደሚፈጽሙ ተመልክቷል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር አምባሳደር ያማማቶ ትላንት እሁድ ኤርትራ ቢገቡም ከኤርትራ ባለስልጣናት ጋር የሚነጋገሩት ዛሬ ሰኞ መሆኑ ታውቋል።

ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ጋር እንደሚወያዩም ተመልክቷል።

አስመራ የሚገኘውን የአሜሪካ ኤምባሲ መጎብኘትም የጉዟቸው አካል እንደሆነም ከዘገባዎች መረዳት ተችሏል።

በአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማት የሚመራው የአሜሪካ ልኡክ ከአስመራ ወደ ጅቡቲ በመሻገር ማክሰኞና ረቡዕ በጅቡቲ ቆይታ ያደርጋሉ።

ሐሙስ ኢትዮጵያ የሚገቡትና ተልዕኳቸውንም እዚያው የሚያጠናቅቁት አምባሳደር ዶናልድ ያማማቶ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ለመነጋገር መርሃ ግብር እንደተያዘላቸውም ተመልክቷል።

በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ተጠባባቂ ረዳት ሚኒስትር ዶናልድ ያማማቶ የሚመራው ልኡክ ወደ ኢትዮጵያና ኤርትራ ጉዞውን ያደረገበት ምክንያት ግልጽ አልሆነም።

የጅቡቲ ጉዞው ግን የአሜሪካና የጅቡቲ ባለስልጣናት አመታዊ ፎረም ላይ ለመገኘት እንደሆነ መረዳት ተችሏል።

የአሜሪካ ጅቡቲ አመታዊ የውይይት መድረክ በኢኮኖሚ፣ጸጥታና እርዳታ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር እንደሆነም መረዳት ተችሏል።

በአሜሪካው ከፍተኛ ባላስልጣናት ዶናልድ ያማማቶ የኢትዮጵያና ኤርትራ ጉዞ በሁለቱ ሃገራት ውዝግብ ላይ ያተኮረ እንደሆነ በአንዳንድ ሪፖርቶች ላይ ተመልክቷል።

ትክክለኛው ምክንያት ግን በይፋ አልታወቀም።

ባለፈው ሕዳር አሜሪካ የሁለቱን ሀገራት ማለትም የኢትዮጵያ ኤርትራን ውዝግብ ለመፍታት እየሞከረች ነው ማለታቸው ይታወሳል።

ዶናልድ ያማማቶ በኢትዮጵያና ጅቡቲ በአምባሳደርነት ኤርትራ ውስጥ ደግሞ በጉዳይ ፈጻሚነት አገልግለዋል።