የሰላም ባስ አውቶብስ በህዝብ ተቃውሞ እንዳይንቀሳቀስ ተደረገ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 26/2010)

በሰሜን ሸዋ አጣዬ የሰላም ባስ አውቶብስ በህዝብ ተቃውሞ እንዳይንቀሳቀስ ተደረገ።

ከትላንት በስቲያ የሆነው ዛሬም ድረስ አልበረደም።

የአጣዬን ከተማ መሃል ለመሃል የሚከፍለው ድልድይ ላይ የተጀመረው ተቃውሞ ሰፍቶ በፌደራል ፖሊስና በታጠቁ ሃይሎች መካከል ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ እንደተካሄደ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

መነሻው ድልድዩን ሊያቋርጥ የተቃረበን የሰላም ባስ አውቶብስን ነዋሪው በማስቆሙ ነው።

ምክንያቱ ደግሞ የህዝብ ሀብት ተዘርፎ የተመሰረተው የትግራይ መልሶ ማቋቋሚያ ድርጅት ኢፈርት ንብረት የሆነው የሰላም ባስ አውቶብስ ላይ ተቃውሞ ለማሳየት እንደሆነ ከአካባቢው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ህዝቡ የሰላም ባስ አውቶብስ የአጣዬን ድልድይ እንደተቃረብ እንዳይሻገር ማገቱ የተገለጸ ሲሆን ፌደራል ፖሊስ ተኩስ በመክፈት ለመበተን ላደረገው ጥረት የአጸፋ ምላሽ እንደተሰጠው ለማወቅ ተችሏል።

ህዝቡ በድንጋይና የታጠቀው በመሳሪያ ከፌደራል ፖሊስ ጋር መግጠሙንም በመረጃው ተመልክቷል።

ስለደረሰው ጉዳት የታወቀ ነገር ባይኖርም እስከዛሬ ድረስ ውጥረት እንዳለ ታውቋል።

የሰላም ባስ አውቶቡስ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በተነሱት ህዝባዊ ተቃውሞዎች የጥቃት ዒላማ ሆኗል።

በቅርቡ በወሎ፣ ውጫሌና ኦርጌሳ የሰላም ባስ አውቶቡሶች ላይ ጥቃት የተፈጸመ ሲሆን ባለፈው ሳምንትም በጭሮ አሰበ ተፈሪ አራት የሰላም ባስ አውቶብሶች በተቃውሞ መሰባበራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በተያያዘ ዜና በምዕራብ ጎጃም ፍኖተ ሰላም ከተማ የህወሀት ሰላይ ነው የተባለ ግለሰብ በትላንትናው ዕለት በጥይት ተመቶ መገደሉን መረጃዎች አመለከቱ።

በኤርትራ የሚንቀሳቀሰው የአማራ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሃላፊነቱን እወስዳለሁ ብሏል።

አዴሃን እንዳስታወቀው መምህርነትን በሽፋን በመጠቀም ላለፉት ሰባት ዓመታት ለህወሀት በመሰለል በርካታ የአማራ ተወላጆችን ሲያሳስርና ሲያስገድል የነበረው መኮንን ትዕዛዙ በፍኖተ ሰላም ከተማ ቄራ ሰፈር በሚባል አካባቢ በታጣቂዎች ተገድሏል።

ይህንን ዘገባ በማረጋገጥ የአማራ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ያወጣው መግለጫ ላይ እንደተመለከተው መምህር መኮንን ትዕዛዙን የገደሉት ታጣቂዎች መያዛቸውን አስታውቋል።

የአማራ ክልል መንግስትም በመምህሩ ግድያ የተሰማውን ሀዘን ይገልጻል ሲል ኮሚኒኬሽን ቢሮው የጠቀሰ ሲሆን በክልል መንግስት ደረጃ የሀዘን መግለጫ የተላለፈለት ግለሰብ ከመምህርነት ያለፈ ቁልፍ ሰው እንደነበር የሚያመላክት ነው ሲሉ ታዛቢዎች ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በወለጋ ደምቢ ዶሎ ትላንት የተነሳውን ተቃውሞ ለመበተን የአጋዚ ወታደሮች ህዝቡ ላይ ቦንብ መወርወራቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ስርዓቱን ለማውገዝ በተጠራው የተቃውሞ ትዕይንት ላይ በተወረወረው ቦንብ ከ20 በላይ ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን በህይወት ላይ የደረሰ የሞት አደጋ ስለመኖሩ የታወቀ ነገር የለም።

በደርባን ሲሚንቶ ፋብሪካ ባለፈው ሳምንት የተጀመረው የስራ ማቆም አድማ መቁጠሉም ታውቋል። አምስተኛ ቀኑን ያስቆጠረው የስራ ማቆም አድማን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት እየሞከርን ነው።