እስረኞቹን ለመልቀቅ ዝግጅት በመደረግ ላይ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 27/2010)

በኢትዮጵያ ወህኒ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ፖለቲከኞችን ለመፍታት በኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ እስረኞቹን ለመልቀቅ ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑን ለስርአቱ ቅርበት ያላቸው መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።

አንዳንድ የሕወሃት ደጋፊዎች እስረኞቹን ለመፍታት የተደረሰው ስምምነትን በመቃወም ላይ መሆናቸውን ሰምተናል።

የሕወሃት መሪዎችም የተወሰኑ የፖለቲካ እስረኞች እንዳይፈቱ በመከላከል ላይ መሆናቸውን ምንጮች ገለጸዋል።

የኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ 18 ቀናት ያህል ባደረገው ስብሰባ እንደተወሰነ የተገለፀው እስረኞችን የመፍታቱ ርምጃ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ጭምር ድጋፍ ያገኘ ቢሆንም አፈፃጸሙ ግን ከወዲሁ ሣንካ እንደገጠመው በመገለጽ ላይ ነው።

የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ መሪዎች በተለይም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ሃላፊው አቶ ጌታቸው አሰፋ ኮለኔል ደመቀ ዘውዱን ጨምሮ የተወሰኑ እስረኞች እንዳይፈቱ በመከላከል ላይ መሆናቸው ታውቋል።

የብአዴን መሪዎች ደግሞ ኮለኔል ደመቀን አለመፍታት ችግሩን እንደሚያባብስና እንደሚያወሳስብ በማሳሰብ ላይ መሆናቸውንም የቅርብ ምንጮች ገልፀዋል።

በቀድሞው የሕወሃት አባል በአቶ አማረ አረጋዊ ባለቤትነት ስር ያለው ሪፖርተር እስረኞቹን እስከ ነገ ታህሳስ 28/2010 ለመፍታት እንቅስቃሴ መጀመሩን ይፋ አድርጓል።

የወህኒ ቤት ሃላፊዎች የተፈረደባቸውን እስረኞች ዝርዝር እንዲያቀርቡ አቃቤ ህግም በተመሳሳይ ክሳቸው በሂደት ላይ ያለ ግለሰቦችን ዝርዝር እንዲሰጥ መታዘዙንም ዘገባው አስፍሯል።

በሌላም በኩል በዝዋይና ሸዋሮቢት የሚገኙ የፌደራል እስረኞች ከዛሬ አርብ ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ እንዲንቀሳቀሱ መወሰኑም ተሰምቷል።

የተለየ ሁኔታ ካልተፈጠረ በቀር በሚሊኒየም አዳራሽ በሚካሄደው የሙዚቃ ፕሮግራም የፍቺውና የስንብት ስነ-ስርዓቱ እንደሚካሄድም ተመልክቷል።

ከሚለቀቁት እስረኞች ውስጥ የተመረጡ ሰዎችን ጨምሮ ፕሬዝዳንቱ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ መርሐ ግብር እንደተያዘም የቅርብ ምንጮች ገልጸዋል።

በህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ደጋፊዎች ዘንድ ባለው ኩርፊያና ጫጫታ- ፕሮግራሙ በታቀደው መሰረት ላይካሄድ ይቻላል የሚል ጥርጣሬ አሳድሯል።

የፖለቲካ እስረኞቹን ለመፍታት የተደረሰው ውሳኔ በህዝባዊ ወያኔ ሐርነት ደጋፊዎች ዘንድ የተጠበቀውን ያህል ድጋፍ አላስገኘም ይልቁንም ተቃውሞዎች እየቀረቡ መሆናቸው ታውቋል።

አቅም የለንም ወይ? ተገዶ ነው እንዴ? የምንፈታቸው የሚሉ ጥያቄዎች በሕወሃት ደጋፊዎች ዘንድ በመሳት ላይ መናቸውም ተመልክቷል።

በማህበራዊ ድረ ገጾች በግልፅ በተፃፉ የህውሃት ደጋፊዎች መልዕክት በኦሮሚያ ክልል በቅርቡ ሰላይ ናችሁ ተብለው የታሰሩ የትግራይ ተወላጆችን ያልጨመረ የመፍታት ሂደት ተቀባይነት እንደማይኖረው ፅፈዋል።

በኦሮሚያ ክልል የታሰሩና የተፈረደባቸው የትግራይ ተወላጆች ሳይፈቱ ሌሎቹን ብቻ መልቀቅ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሒውማን ራይትስ ዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ ዘረኛ ውሳኔ ነው በማለት አሳስበዋል።

ይህ ሳይሆን እስረኞቹን ለመፍታት የሚደርገው ጥድፊያ ብሔራዊ መግባባት ከመፍጠር ይልቅ የዓለም አቀፉን የገንዘብ ተቋም ግፊት ለማስተናገድ የሚደረግ ሽርጉድ ነው ሲሉም ተችተዋል።

የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ማኔጂንግ ዳይሬክተር በቅርቡ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት የሃገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታን አሳሳቢነት ጠቅሰው መፍትሄ እንዲገኝ ማሳሰባቸውንም መረዳት ተችሏል።