በትራምፕና በቤተሰቦቻቸው ዙሪያ የተፈጸሙ የተለያዩ ቅሌቶችን አንድ መጽሀፍ አጋለጠ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 26/2010)

በአንድ ጋዜጠኛ ተጽፎ በቅርቡ ለገበያ የሚቀርበው መጽሀፍ በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕና በቤተሰቦቻቸው ዙሪያ የተፈጸሙ የተለያዩ ቅሌቶችን አጋለጠ።

መጽሀፉ የተለያዩ ሚስጥሮችን ማጋለጡ ቀድሞውንም በቀውስ የተሞላውን ኋይት ሀውስ የበለጠ ነዳጅ ቸልሶበታል።

መጽሀፉ ዋና መነጋገሪያ ከሆነባቸው ጉዳዮች አንዱ የቀድሞው የኋይት ሀውስ ዋና ዕቅድ ነዳፊ ስቲቭ ባነን በሰኔ ወር 2016 በትራምፕ ልጅና በሩሲያ መንግስት ሰዎች መካከል በትራምፕ ህንጻ ውስጥ የተደረገው ውይይት እንደ ሀገር ክህደት ይቆጠራል ማለታቸው ነው።

“ፋየር እና ፊዩሪ” በግርድፍ ትርጉሙ “እሳትና ቁጣ” የትራምፕን ኋይት ሃውስ ጓዳ ይፈትሻል።

ማይክል ዎልፍ በተባለ ጋዜጠኛ የተጻፈው ይህ መጽሃፍ እንደሚለው ገና ከጅምሩ ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ማሸነፋቸው እራሳቸውን እጅግ ግራ ያጋባቸው ጉዳይ ነበር ብሏል።

ትራምፕ የፕሬዝዳንታዊ ሹመት ስነ ስርአቱን እንዳልተደሰቱበትና በአንዳንድ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች ዘንድ እንደ እስር ቤት የሚቆጠረው ኋይት ሃውስ መግባቱም እጅግ ያስፈራቸው ጉዳይ ነበር ብሏል መጽሀፉ።

ታዋቂ አሜሪካውያን በሹመት ስነስርአቱ ላይ በተቃውሞ አለመገኘታቸውም እጅግ ያስቆጣቸው ጉዳይ ነበር።

መጽሀፉ በተለይ የፕሬዝዳንቱ ልጅ ከሩሲያ ጠበቆችጋ ኒዮርክ በሚገኘውና ትራምፕ ታወር ተብሎ በሚታወቀው በአባቱ ሕንጻ ውስጥ ስብሰባ መቀመጣቸው የሀገር ክህደት ነው ማለቱ በጉዳዩ ላይ እየተደረገ ያከው ምርመራ በጦዘበት ሰአት መሆኑ በአሜሪካውያንና በመገናኛ ብዙሃን ዘንድ ከፍተኛ ትኩረትን አግኝቷል።

ሌላው በመጽሀፉ የተጋለጠው ጉዳይ ደግሞ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከጓደኞቻቸ ሚስቶችጋ መማገጣቸውን በኩራት የሚያወሩት ጉዳይ መሆኑ ነው።

የጓደኞቻቸው የትዳር አጋሮችጋ ከትዳር ውጪ ግንኙነት ማድረጋቸው ለእሳቸው ሕይወት የበለጠ ትርጉም እንደሰጣቸውና ሕይወትን እንዲወዱት ምክንያት እንደሆናቸው ተናግረዋል ብሏል መጽሀፉ።

የትራምፕ የመጀመሪያ ሴት ልጅ ኢቫንካ ትራምፕ ፕሬዝዳንት የመሆን ሕልም እንዳላት በመጽሀፉ መገለጹ ደግሞ ሌላው ነው።

ኢቫንካና ባለቤቷ ጃሬድ ኩሽነር እሷ ወደፊት ለፕሬዝዳንትነት መወዳደር እንዳለባት ተማምነው በኋይት ሃውስ በተለምዶ የምዕራብ ክንፍ ተብሎ በሚጠራው ቢሮ በቋሚነት መስራተ ጀመሩ።

አጋጣሚው የሚፈጠር ከሆነም የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ኢቫንካ እንጂ ሒላሪ ክሊንተን እንደማትሆን ዝተዋል ይላል መጽሀፉ።

ይህ ሃሳባቸውም ስቲቭ ባነንን እጅግ እንዳስቆጣ ተጠቅሷል።

ኢቫንካ በአባቷ ጸጉር አያያዝ እጅግ ትሳለቅ እንደነበርና ፕሬዝዳንቱ ጸጉር የሌለው የመሃል አናታቸው ቆዳ በቀዶ ጥገና ከወጣ በኋላ በየጥጉ የበቀለው ጸጉር ወደ መሃል ተስቦ በማጣበቂያ ኬሚካል እንዲለጠፍ ይደረጋል ስትል በአሜሪካውያን ዘንድ እንቆቅልሽ የሆነውን የፕሬዝዳንቱን ጸጉር ሚስጥር አጋልጣለች።