የሪፖርተር ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ታስሮ ወደ ደቡብ ክልል ተወሰደ

መስከረም (ላሳ)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-ጋዜጣው እንደዘገበው  መላኩ ደምሴ  ሐሙስ መስከረም 30 ቀን 2006 .. እኩለ ቀን ላይ አዲስ አበባ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ ከሚገኘው የሪፖርተር ቢሮው በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል የፖሊስ ኃይል አባላት ተይዞ ወደ ሐዋሳ ከተማ ተወሰዷል፡፡

ጋዜጠኛው ለጥያቄ የተወሰደው ሪፖርተር ጋዜጣ ረቡዕ ነሐሴ 29 ቀን 2005 ዓ.ም. በጋዜጣው የፊት ገጽ ላይ ‹‹የደቡብ ክልል ሦስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሮች ከኃላፊነት ተነሱ›› በሚል ባተመው ዜና ምክንያት ነው።

አዘጋጁ በቅድሚያ አምቼ አካባቢ በሚገኘው በቦሌ ክፍለ ከተማ በፖሊስ ማዘዣ የተወሰደ ሲሆን፣ በኋላም ለክልሉ ፖሊስ አባላት ተላልፎ መሰጠቱን ጋዜጣው ዘግቧል፡፡

የክልሉ ኃላፊዎቹ ተነስተዋል በሚል ሪፖርተር ጋዜጣ የዘገባው ዜና ስህተት መሆኑን በማመን በቀጣይ ዕትሙ እሑድ ጳጉሜን 3 ቀን 2005 ዓ.ም. ላይ ዜናው በወጣበት የጋዜጣው የፊት ገጽ ላይ ማስተካከያ ማውጣቱን ጠቅሷል።

በሐዋሳ የሚገኘው የሪፖርተር ባልደረባም ይህንን ዘገባ በማጠናቀርና በመዘገብ ለሠራው ስህተት ዝግጅት ክፍሉ አስተዳደራዊ ዕርምጃ መውሰዱን አክሎ ገልጿል፡፡ በተመሳሳይ ዜናም  የሊያ መጽሔት አዘጋጆች በባለሀብትም፤በህግም በደል እንደተፈጸመባቸው ገለጸዋል።

ከባለስልጣናት ጋር ግንኙነት ባለውና በ አጭር ጊዜ ውስጥ  ከፍተኛ ባለሀብት በሆነ ግለሰብ  የ 36 ሺህ ብር የማስታወቂያ ክፍያ የተከለከሉ የሊያ መጽሔት አዘጋጆች፤ ይባስ ብሎ “የባለሀብቱን ስም አጥፍታችሁዋል” ተብለው  ማዕከላዊ ፖሊስ ቃል ከሰጡ በሁዋላ በዋስ መለቀቃቸው ተገልጿል።

አዲስ አበባ የሚገኘው የ ኢሳት ዘጋቢ እንዳጠናቀረው መረጃ  በ አጭር ጊዜ በመተኮስ የ አሉሙኒየም ፋብሪካ ባለቤት የሆነው ባለሀብት ከሊያ ጋዜጣ ጋር በመስማማት ለረዥም ጊዜያት ስለ ድርጅቱ ማስታወቂያ ሢያሰራ ቆይቷል።

ይሁንና በቅርቡ የማስታወቂያውን ክፍያ እንዲፈጽሙ በጋዜጣው ሲጠየቁ  ከፍላጎቴ ውጪ የሆነ ነገር ወጥቷል በመል ምክንያት  ክፍያውን ለመፈጸም ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ያመለከተው የሪፖርተራችን ዘገባ፤ጋዜጠኞቹ ክፍያው እንዲፈጸምላቸው ጥያቄ ሲያቀርቡላቸው፦”አርፋችሁ ተቀመጡ፤አምስት ሳንቲም አልሰጣችሁም። አርፋችሁ የማትቀመጡ ከሆነ እጄ ረዥም መሆኑን አሳያችሁዋለሁ” ብለው እንደዛቱባቸው ያሳያል።፣

በተፈጸመባቸው ክህደት  ያዘኑት የሊያ መጽሔት አዘጋጆች በመጽሔቱ ቅጽ 2 ቁጥር 35 ህትመት ላይ” እጄ ረዥም ነኝ ባዩ ባለሀብት ገመና ሲፈተሽ”በሚል ርዕስና በመስከረም  18/2006 ዕትም   ስለባለሀብቱ የምርመራ ዘገባ ከመስራታቸውም በላይ የደረሰባቸውን ነገር በዝርዝር የገለጹ ሲሆን፤ በዚህም ጽሑፍ ሳቢያ በባለሀብቱ የስም ማጥፋት ክስ ተመስርቶባቸው  ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ቀርበው የመኪና ሊብሬ እና የንግድ ፈቃድ በማስያስ በዋስ ተለቀዋል።

አንድ የሕትመት ውጤት የስም ማጥፋት ወንጀል በማድረስ ከተጠረጠረ ፖሊስ የሚጠራውም ሆነ ክስ የሚመሠረትበት፣ ዋና አዘጋጁና ዘጋቢው መሆኑን የገለጹት የመጽሔቱ ማኔጂንግ ኤዲተር አቶ መላኩ አማረ፣ በፕሬስ ታሪክም ሆነ በኢትዮጵያ ሕግ ተፈጽሞ ወይም ተሞክሮ የማያውቅ ድርጊት በሊያ መጽሔት አዘጋጆች፣ ዓምደኞች፣ አሳታሚና አታሚ ላይ መድረሱ እንዳስገረማቸው ተናግረዋል፡፡

በመጽሔቱ የተስተናገደው መጣጥፍ ትክክል ካልሆነም አግባብ ባለው የሕግ ሒደት መጠየቅ ሲገባ፣ የአንድ መጽሔት አዘጋጆችን ዓምደኞችን፣ አሳታሚ ድርጅትንና አታሚን በጅምላ መክሰስ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ስሜና የድርጅቴ ስም ጠፍቷል›› በሚል ለፖሊስ ያመለከቱት ግለሰብ፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት “እጄ ረዥም ነኝ”በማለት  ሲዝቱባቸው የነበረውን በተግባር ተርጉመው በማሳየታቸው ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘመዴ ነው፤ የደኅንነት ኃላፊው ጓደኛዬ ነው፡፡ ዛሬ ከከንቲባ እከሌ ጋር ምሳ በላን፤ ነገ ከጄነራል እከሌ ጋር ቀጠሮ አለኝ…›› በማለት የቢዝነስ አጋሮቻቸውንና ሌሎች የሚቀርቧቸውን ግለሰቦች ወይም አበዳሪና ተበዳሪ አካላትን በማስፈራራት፣ የማጭበርበር ወንጀል የሚፈጽሙ በርካታ ሀብታም ነን ባዮች መኖራቸውን የገለጹት አቶ መላኩ፣ የእነሱ መጽሔትም ሆነ ሌሎች የሕትመት ውጤቶች ምርመራ በማድረግና የእነዚህን እጀ ረዣዥምና ሀብታም ነን ባዮችን ሥራዎቻቸውን ማጋለጥ አንዱ የጋዜጠኛ ሥራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት አንድን የፕሬስ ውጤት ማገድ ወይም ማስቆም የሚችሉት ፍርድ ቤት ወይም ፍትሕ ሚኒስቴር መሆኑን የጠቆሙት አቶ መላኩ፣ ይህም ቢሆን ተገቢ ያልሆነ ሪፖርት ሲሰራጭ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሊያ መጽሔትና አዘጋጆቹ፣ ዓምደኞቹ፣ አሳታሚውና አታሚው ስም በማጥፋት ወንጀል የተጠረጠሩት በአቶ ቴዎድሮስ በለጠና በድርጅታቸው ኢትዮ አልሙኒየም ካምፓኒ ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ መላኩ፣ በመጽሔቱ ላይ የሰፈሩት መጣጥፎች በመረጃ ላይ የተመሠረቱ ብቻ ሳይሆኑ በማስረጃ በደንብ የተደገፉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስለ ጉዳዩ ባለሀብቱን  አቶ ቴዎድሮስ በለጠን ለማነጋገር የተደረገው ጥረት አልተሳካም።