(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 14 /2010 ) የሼህ መሃመድ አላሙዲን ንብረት የሆነው ሜድሮክ ጎልድ እንዲሁም የሕወሓት ንብረት የሆነው ኢዛና ጎልድ ከቤሄራዊ ባንክ መመሪያ ወጭ በልዩ ድጋፍ ወርቅ ሲሸጡ መቆየታቸው ተገለጸ።
በሌላም በኩል የብሄራዊ ባንክ ገዢው አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ከብር ምንዛሪ ለውጥ ጋር በተያያዘ መገምገማቸው ታወቀ ።ቤተሰቦቻቸውንም ወደ አሜሪካ አሽሽተዋል።
የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ሜድሮክ ጎልድ ባለፉት 20 ዓመታት ከሻኪሶ የሚያወጣውን ወርቅ በብሄራዊ ባንክ በኩል ማስተላለፍ የሚገባው ቢሆንም በልዩ ትዕዛዝ በቀጥታ ሲሸጥ መቆየቱ ተመልክቷል።
በዚህም ለተወሰኑ ግዚያት በተላያዩ መጠኖች ስለ ሽያጩ ለብሄራዊ ባንክ ሪፖርት ያደረገ ቢሆንም፣አጠቃላይ የንግድ ሂደቱን የተመለከተ መረጃ ግን በብሄራዊ ባንክ እንደማይገኝ ከኢሳት ምንጮች መረዳት ተችሏል።
የንግድ ልውውጡ ለምን በብሄራዊ ባንክ በኩል አልሆነም በሚል ከሚመለከታቸው የባንኩ ባለሙያዎች ለሚቀርበው ጥያቄ የብሄራዊ ባንክ ገዢው አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ተዉኣቸው በሚል ይከላከሉ እንደነበርም ተመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ንብረት የሆነው እና ከኤፈርት ተቋማት አንዱ የሆነው ኢዛና ጎልድ በሕገወጥ መንገድ ወርቅ ከሃገር እያወጣ መሆኑንም ምንጮች ገልጸዋል።
ኢዛና የተባለው የሕወሃት ኩባንያ የተመዘገበው በሃገር ውስጥ የንግድ ኩባንያነት ቢሆንም ፣በቀጥታ ወርቅ ወደ ወጭ እንዲልክ ተፈቅዶለታል።
በብራዊ ባንክ መመሪያ መሰረት የሃገር ውስጥ ኩባንያ ወርቁን ለብሄራዊ ባንክ ማቅረብ የሚጠበቅበት ሲሆን፣የሕወሓት ንብረት የሆነው ኢዛና ግን ራሱ ወርቁን ወደ ውጭ አውጥቶ እንዲሸጥ ተፈቅዶለታል።
ገቢውንና የተገኘውን የውጭ ምንዛሪ በተመለከተ ብሄራዊ ባንክ መረጃ እንደማይቀርብለትም መረዳት ተችሏል።
ሜድሮክ ጎልድ ላለፉት 20 ያህል ዓመታት ወርቅ ሲያውጣበት በነበረው ሻኪሶ በገጠመው ተቃውሞ ፈቃዱ ለግዜው መታገዱ ይታወቃል።የሕውወሃቱ ኢዛና ጎልድ አሁንም በስራ ላይ ይገኛል።
በሌላ ዜና በኢትዮጵያ በዚህ ዓመት መጀመሪያ የተካሄደው የብር ምንዛሪ ለውጥ በሃገሪቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ አስከትሏል በሚል በኢሕአዴግ የተገመገሙት የብሄራዊ ባንክ ገዢው አቶ ተክለወልድ አጥናፉ መላ ቤተሰባቸውን ወደ አሜሪካ መላካቸውን ምንጮች ገለጹ ።
የብር ምንዛሪው ለውጥ በቂ ጥናት አልተደረገበትም በሚል ከወር በፊት በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ የተገመገሙት አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ፣ የመጨረሻው ውሳኔ ላይ የተደረሰው አቶ ኃይለማርያም በመስማማታቸው ነው በሚል ሃላፊነቱን ወደ አቶ ኃይለማርያም ማሻገራቸውን መረዳት ተችሏል።
በብሄራዊ ባንክ ገዢነት ረዥም ዓመታት የቆዩት አቶ ተክለወልድ አጥናፉ በስራቸው ውጤታማ አይደሉም በሚል እየተወቀሱ ሲሆን፣በቅርቡ ከኃላፊነት ከሚነሱ ባለስልጣናት አንዱ እንደሚሆኑም እየተገለጸ ይገኛል።
አቶ ተክለወልድ አጥናፉ መላ ቤተሰባቸውን ወደ አሜሪካ ያሸሹበት ምክንያት አልታወቀም።
ቤተሰቦቻቸው ከሃገር የወጡት ከሶስት ወር በፊት እንደሆነም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
የብሄራዊ መረጃ እና ደህነነት ዋና ሓላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ መላ ቤተሰባቸውን ወደ አሜሪካ ማሸሻቸውን ትናንት መዘገባቸን ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የቀድሞ የገንዘብ እና የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ አቶ ሶፍያን አህመድ ከሃገር ከወጡ አንድ ዓመት አልፏቸዋል።
ነዋሪነታቸውንም ከነ ቤተሰባቸው ካናዳ ያደረጉት አቶ ሶፍያን አህመድ ከሃገር የወጡት የመስሪያ ቤታቸው የስራ ሃላፊዎች በሙስና መታሰራቸውን ተከትሎ እንደሆነም ተመልክቷል።