የሶማሌ ክልል የሃገር ሽማግሌዎችን ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ነው

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 14/2010) የሕወሃት ጄኔራሎች ለአቤቱታ አዲስ አበባ የገቡትን የሶማሌ ክልል የሃገር ሽማግሌዎችን እያስፈራሩ መሆኑ ታወቀ።

የሃገር ሽማግሌዎቹ ከአዲስ አበባ እንዲወጡ ጫና እያደረጉ መሆኑም ታውቋል።

የአብዲ ኢሌ አስተዳደር ለሕወሃት ጄኔራሎችና ለደህንነቶች ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ ሽማግሌዎቹ ወደ ሶማሌ ክልል እንዲመለሱ ግፊት እያደረገ መሆኑም ተገልጿል።

ከአብዲ ኢሌ በድብቅ ገንዘብ ከተከፈላቸው ጄኔራሎቹ መካከልም ገብሬ ዲላና ማአሾ እንደሚገኙበትም የኢሳት ምንጮች አረጋግጠዋል።

ለአቤቱታ ወደ አዲስ አበባ የተጓዙት የሶማሌ ክልል ሽማግሌዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሳያገኙ አንድ ወር እንዳለፋቸው በምሬት በመገለጽ ላይ መሆናቸውንም መረጃው አመልክቷል።

150 የሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች ለአቤቱታ አዲስ አበባ ከገቡ አንድ ወር አልፏቸዋል። እስከሁን ያናገራቸው የመንግስት ባለስልጣን የለም።

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ደጅ በተደጋጋሚ ቢጠኑም የሚያስጠጋቸው አላገኙም። ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ደግሞ የህወሀት ጄነራሎችና የደህንነት ሰዎች ወከባ ውስጥ ወድቀዋል።

የኢሳት የመረጃ ምንጮች እንደገለጹት የሀገር ሽማግሌዎቹ ለህይወታቸው ስጋት የሚፈጥር ወከባና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ነው።

ለሶማሌ ክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ ኦማር መሀመድ ኢሌ ድጋፍ ለመስጠትና የሽማግሌዎቹን እንቅስቃሴ ለማስቆም በደቡብ ሱዳን የሚገኙት የህወሀቱ ጄነራል ገብሬ ዲላ ሳይቀር አዲስ አበባ መግባቱንም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ጄነራል አብረሃም ወልደማርያም ወይም ኳርተር የተባሉት የህወሀት ከፍተኛ የጦር ሹምም በአብዲ ኢሌ ከፍተኛ ገንዘብ ተከፍሏቸው ሽማግሌዎቹ ላይ የወከባና ማስፈራራት ዘመቻ ከከፈቱት መሃል የሚጠቀሱ ናቸው።

ጄነራል መኦሾም አብዲ ኢሌን ከሽማግሌዎቹ ጫና ለመታደግ መሰለፋቸው ታውቋል።

ሽማግሌዎቹ አቤቱታውን ትተው ከአብዲ ኢሌ ጋር እንዲስማሙ በቅድሚያ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄ ያቀረቡት የህወሀት ጄነራሎችና ደህንነቶች በሽማግሌዎቹ በኩል ተቀባይነት በማጣታቸው ወደግልጽ ማስፈራሪያ እንደገቡ የኢሳት ምንጮች ካደረሱን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

አብዲ ኢሌ ለእናንተም ለእኛም ወሳኝ ሰው ነው፡ የጋራ ጠላታችን ከሆነው የኦሮሞ ህዝብ የሚታደገን አብዲ ኢሌ በስልጣን መቆየት አለበት፡ እናንተም አግዙት የሚለውን የህወሀት ጄነራሎች ግፊት ያልተቀበሉት የሀገር ሽማግሌዎቹ የእኛ ጠላት የኦሮሞ ህዝብ አይደለም፡ ህዝባችንን እያቃየ ያለውን አብዲ ኢሌን በአስቸኳይ ካላነሳችሁት የህዝቡ አመጽ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን እንደሚችል በመግለጽ የቀረበላቸውን ጥያቄ ውድቅ አድርገውታል።

የኢሳት ምንጮች እንደሚሉት አቶ አብዲ ኢሌ የሽማግሌዎችን እንቅስቃሴ እንዲገቱለት ለህወሀት ጄነራሎች በግላቸው ከፍተኛ ገንዘብ ከፍሏቸዋል።

በህወሀት ጄነራሎችና በአብዲ ኢሌ መካከል ያለው ወዳጅነት ከጥቅም የተሳሰረ መሆኑን የሚገልጹት የኢሳት ምንጮች ከበርበራወደብ  ኢትዮጵያን አቋርጦ ደቡብ ሱዳን ጁባ ድረስ የተዘረጋውን የኮንትሮባንድ ንግድ ለሚመሩት የህወሀት ጄነራሎች ወሳኝ ሰው በመሆን እያገለገለ ያለው የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ኢሌ  እንደሆነም ይጠቅሳሉ።

የአብዲ ኢሌ ከቦታው መነሳት ከማንም በላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊሆን የሚችለው ለህወሀት ጄነራሎች መሆኑን ነው ለማወቅ የተቻለው።

በዚህም ምክንያት የአብዲ ኢሌን በስልጣን መቆየት የትኛውንም ሃይል ተጠቅመው የህወሀት ጄነራሎች እየተሯሯጡ ነው ተብሏል።

በአዲስ አበባ የሚገኙት የሀገር ሽማግሌዎች ላይ የሚደረገው ማስፈራሪያ ካልቆመና ሽማግሌዎቹ ወደ ሶማሌ ክልል ከተመለሱ ህዝባዊው ተቃውሞ ከቁጥጥር ሊወጣ እንደሚችል ከወዲሁ ስጋቱ እየተገለጸ ነው።

በሶማሌ ክልል በአብዲ ኢሌ ላይ የተጀመረው ተቃውሞ እንደቀጠለ ሲሆን በእስከሁን ከ20 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ከ1ሺህ በላይ ታስረዋል።