ታህሳስ ፳፮(ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የጁምዓን ጸሎት ተከትሎ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን መንግስት እየሄደበት ያለውን አካሄድ በመተቸት ተቃውሞአቸውን ያሰሙ ሲሆን፣ በሀረር ግጭቱ ተባብሶ አንድ ከ10 እስከ 12 ዓመት የሚገመት እድሜ ያለው ኪያ የሚባል ወጣት ተገድሏል። ሀረር የሚገኙ የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ሙስሊሞች በ4ኛ መስጊድ ተገኝተው ስግደታቸውን ካደረሱ በሁዋላ በሰላም ወደ ቤታቸው ሲመለሱ የፌደራል ፖሊስ አባላት የተወሰኑ ወጣቶችን ለማሰር በመፈለጋቸው ነው ግጭቱ የተፈጠረው።
የፌደራል ፖሊስ አባላት በተኮሱት ጥይት ህጻኑን ከመግደላቸው በተጨማሪ እናቱንም እንዳቆሰሉዋት ለማወቅ ተችሎአል። ሌሎች ሶስት ነዋሪዎችም በጽኑ መቁሰላቸው ታውቋል። በርካታ ወጣቶችም ታፍሰው ወደ እስር ቤት ተወስደዋል። ሁኔታው የተረጋጋ ቢመስልም በህዝቡ ዘንድ የሚታየው ቁጭት እንዳለ በመሆኑ የፌደራል ፖሊስ አባላት አካባቢውን እየተዟዟሩ በመጠበቅ ላይ ናቸው።
በወልድያ ደግሞ የጸጥታ ሀይሎች በርካታ ሙስሊም ወጣቶችን ይዘው አስረዋል። ወጣቶቹ የታሰሩት በአልበሲጥ መስጊድ ስግደት ካደረጉ በሁዋላ ነው። “መሀይም አይመራንም፣ የታሰሩ መሪዎቻችን ይፈቱ “፣ አንዳንድ ወጣቶች ደግሞ ” መንግስት ሊመራ አልቻለም ይወረድ ” የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል። ወጣቶቹ መሀይም አይመራንም በማለት የተናገሩት አዲስ የተመረጡ የመጅሊስ አመራሮችን ነው።
የፌደራል ፖሊስ አባላት በአነስተኛ እና ጥቃቅን የተደራጁ ወጣቶችን በማሰለፍ በሙስሊሞቹ ላይ ጸረ ልማት የሚል ቅስቀሳ ለማካሄድ መሞከራቸውን፣ የወልዲያ ነዋሪዎች ተናግረዋል። በቁጥር ምን ያክል ወጣቶች እንደታሰሩ ለማወቅ ባይችላም፣ በርካታ ወጣቶች በፌደራል ፖሊስ መኪኖች እየተጫኑ ወደ እስር ቤት ተወስደዋል። የሀረርና የወልድያ ፖሊስ አዛዦችን ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።
ታላቁን የአንዋር መስጊድ ጨምሮ በደሴ፣ በአዋሳ፣ በሻሸመኔ እና በአዳማ ( ናዝሬት) ተመሳሳይ የተቃውሞ ድምጾች ተሰምተዋል።
መንግስት የሙስሊሞችን ሰላማዊ ጥያቄ ከሽብርተኝነት ጋር እያያዘ ወደ አልሆነ አቅጣጫ እየገፋው መምጣቱ ብዙዎችን ያሳሳበ ጉዳይ ሆኗል። የአሜሪካ መንግስት መንግስት እየተከተለ ያለው አካሄድ ትክክለኛ አለመሆኑን መግለጹ ይታወሳል።