የሙስሊም መሪዎች የፍርድ ቤት ሂደት ብዙ ጥያቄዎችን እንደሚያስነሳ ሂውማን ራይትስወች ገለጠ

መጋቢት ፳፬ (ሀያ አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 

ኢሳት ዜና:-ድርጅቱ ባወጣው መገለጫ በ29 የሙስሊም መሪዎች ላይ የተጀመረው የፍርድ ሂደት ለ40 ቀናት ከተቋረጠ በሁዋላ ዛሬ የሚጀመር ቢሆንም እስካሁን የነበረው የፍርድ ሂደት ተአማኒ እንዳልነበር ገልጿል።

መሪዎቹ በእስር ቤት እያሉ ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ በቂ የሆነ የህግ አገልግሎት እንዲያገኙ አለመደረጉንና የፍርድ ሂደቱ ከሚዲያ፣ እና ከሌሎች ታዛቢ አካላት ውጭ እንዲካሄድ መደረጉን ጠቅሷል።

የድርጅቱ የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ሌስሌ ሌፍኮው ሲናገሩ የኢትዮጵያ መንግስት የጸረ ሽብር ህጉን ድንበር ሳይገድበው እየተጠቀመበት ነው ብለዋል። አጠቃላይ የፍርድ ቤት ሂደቱም ፖለቲካዊ ይዘት እንዳለው ምክትል ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

መንግስት የጸረ ሽብር ህጉን እንደገና እንዲመረምርና እንዲያሻሽለው፣ ከሙስሊም ኢትዮጵያውያን ጋርም ቁጭ ብሎ በመነጋገር ችግሩን ለመፍታት እንዲሞክር ባለስልጣኑዋ መክረዋል።