የመከላከያ ሰራዊት በቦዲዮች ላይ ተኩስ ከፍቶ በርካታ ሰዎችን ማቁሰሉን ከአካባቢው የደረሰን መረጃ አመለከተ

መጋቢት ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መጋቢት 24 ቀን በቦዲዎችና በኮንሶዎች መካከል ለአንድ ወር ያክል የቆየውን ግጭት ለማብረድ በሚል ወደ አካባቢው የተጓዘው የመከላከያ ሰራዊት በቦዲዎች ላይ በመትረጊስ የታገዘ ተኩስ በመክፈቱ በርካታ ነዋሪዎች መቁሰላቸውን ከእነዚህም ውስጥ 17 አሮጊቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች በሃና ጤና ጣቢያ በህክምና ላይ እንደሚገኙ ጂንካ የሚገኘው የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት ጽ/ቤት ለኢሳት ገልጿል።

የመከላከያ ሰራዊቱ የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ በሰላማጎ ወረዳ አስተዳዳሪና ምክትል አስተዳዳሪ በአንድ ወገን የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊው አቶ ስጦታው በሌላ ወገን ሆነው እየተወዛገቡ መሆኑ ታውቋል።

የኮንሶ የአገር ሽማግሌዎች በበኩላቸው ” ወደዚህ አካባቢ አምጥታችሁት ስታሰፍሩን ከህዝብ ጋር ተመካክረናል፣ ሰላም ነው ብላችሁ ቢሆንም፣ ከመጣን በሁዋላ ግን ለተደጋጋሚ ግጭት ተዳርገናል። ይህም ሆኖ ግችቶችን በጋራ በአገር ባህል መሰረት እየፈታንና እያስተናገድን ባለንበት ጊዜ ይህን አይነት አሰቃቂ እርምጃ መውሰድ ከእንግዲህ ወዲያ አብሮ ለመኖር ያለንን ተስፋ የሚያጨልመው” ነው በማለት መናገራቸውን ድርጅቱ ገልጿል።

የጽ/ቤቱ ሰራተኞች ሆስፒታል ድረስ ሄደው የቆሰሉ ኮንሶዎችና ቦዲዎችን ጎብኝተዋል።

በቦዲና ወደ አካባቢው ሄደው እንዲሰፍሩ በተደረጉት ኮንሶች መካከል በሚደርሰው ተደጋጋሚ ግጭት እስካሁን 4 ኮንሶዎችና 2 ቦዲዎች እንዲሁም አንድ ሾፌር  ተገድለዋል። 3 ኮንሶችና 1 ፖሊስ ሲቆስሉ 72 ቤቶች መቃጠላቸውን፣ ሰውናርድበጊዮ መንደር ደግሞ 1 የማዳበሪያ መጋዘን ከነማዳበሪያዎቹ መቃጠሉን ድርጅቱ በላከው መረጃ አመልክቷል።

በግጭቱ ሳቢያ ለተፈናቀሉ ኮንሶዎች እርዳታ ለማድረስና ለማከፋፈል ወደ ስፍራው ያቀናው ሾፌር ብርሃኑ ማሞ ከምሽቱ 1 ሰአት ላይ ሰውነቱን ወንዝ ዳር ቆሞ እየታጠበ ባለበት ጊዜ ማንነቱ ባልታወቀ ሰው በተተኮሰ ጥይት ተግደሎ አስከሬኑ አዋሳ ውስጥ ተልኮ ተቀብሯል።

አካባቢው አሁንም በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ መሆኑን ድርጅቱ አክሎ ገልጿል። በጉዳዩ ዙሪያ የአካባቢውን ባለስልጣናት ለማነጋገር ያደርግነው ሙከራ አልተሳካም።