የመሬት ቅርምት ወደ ግጭት ሊያመራ እንደሚችል አንድ ታዋቂ ጋዜጣ ዘገበ

ግንቦት ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በስዊዘርላንድ የሚታተም ታገስ አንዛይገር የተባለ ጋዜጣ  ፣ በመሬት እና ባካባቢው ከሚኖሩ ዜጎች ፍላጎት እና ስምምነት ውጭ የሚደረግ ማንኛውም ኢንቨስትመንት  በባለሃብቶች እና ባካባቢው በሚኖሩ ዜጎች መካከል በሚፈጠር  አለመግባባት ወደ ከፍተኛ ግጭት ሊያመራ እና   በሃገሪቷ ውስጥም አለመረጋጋት ሊፈጥር እንደሚችል አስጠንቅቋል።

ጋዜጣው የአቶ መለስ ዜናዊ አስተዳደር ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የእርሻ መሬት 10% ወይም 3.6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለውጭ ባለሀብቶች እንደተሰጠ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ እና በሌሎች ደሀ አገሮች  የሚኖሩ አነስተኛ ገበሬዎች    ህይወታቸውን መሰረት ያደረጉበት መሬታቸው ለውጭ ባለሀብቶች በመቸብቸቡ እና ከቀዬአቸውም እየተፈናቀሉ መሆናቸው የወደፊት መጻኢ እድላቸው አደጋ የተጋረጠበት ነው ሲል አስፍሯል።

ታገስአንዛይገር በመቀጠል በአለም ዙሪያ በተለይ በታዳጊ ሀገሮችና ባላደጉ ሀገሮች ላይ እየተካሄደ ያለውን መሬት ነጠቃ በግንባር ቀደምትነት የምትመራው  ቻይና ናት ብሎአል።

ይህ መሬት ነጠቃም በዋናነት ያተኮረው ባላደጉ ሀገሮች ላይ እና ጠንካራ የመሰረተ ልማት አገልግሎት በሌለባቸው ረሀብና ድህነት በከፍተኛ ደረጃ በሚያጠቃቸው እንዲሁም መንግስት ለዜጎቹ መብት በማይጨነቅባቸው ሀገሮች ላይ እንደሆነ የጠቆመው ጋዜጣው፣ ባለሀብቶቹም በነዚህ ሀገሮች ላይ በከፍተኛ ደረጃ በማተኮር ገንዘባቸውን በማፍሰስ ላይ መሆናቸውን ከላንድ ማትሪክስ ጥናት ለመረዳት ተችሏል በማለት ገልጿል።

ጋዜጣው በአሁኑ ወቅት እየተስፋፋ ያለው የመሬት ቅርምት ካልተገታ በታዳጊ እና በማደግ ላይ ባሉ ሃገራት ውስጥ በሚገኙ አነስተኛ ገበሬዎች የወደፊት ህይወት ላይ ከፍተኛ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል አሳስቦአል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide