ኢትዮጵያዊቷ በኩዌት ጎዳናዎች ራቁቷን ደም በደም ሆና ታየች

ግንቦት ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ደሟን እያዘራች ራቁቷን በኩዌት ጎዳናዎች ላይ ስትሮጥ የነበረች ኢትዮጵያዊት ሴት በፖሊስ ተይዛ -በሳይካትሪስት ምርመራና ህክምና እንዲደረግላት ወደ ሆስፒታል መግባቷን አረብ ታይምስ ዘገበ።

አረብ ታይምስ ፦ “አል ራይ” የተባለውን የአገሪቱን ሳምንታዊ ጋዜጣ ጠቅሶ እንደዘገበው፤ በጎዳና ላይ ሲጓዙ የነበሩ እግረኞች  አፍሪካዊ መልክ ያላት ሴት ራቁቷን ሆና ደም እየፈሰሳት በጎዳና ላይ ስትሮጥ ማየታቸውን ለኩዌት የአገር ውስጥ ሚኒስቴር የኦፕሬሽን ዲፓርትመንት ሪፖርት ያደርጋሉ።

መረጃው የደረሳቸው የኩዌት ደህንነቶችም ወዲያው በመሰማራት  በጎዳና ላይ እርቃኗን ሆና ደሟን የምታዘራውን ሴት ይይዟታል።

በተደረገው ምርመራ ሴቲቱ በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ ስትሠራ የነበረች ኢትዮጵያዊት  ሆና መገኘቷን ይፋ ያደረጉት የደህንነት ምንጮች፤ ደም  ሲፈሳት የነበረውም የገዛ እጇን በስለት በማረዷ እንደሆነ   አመልክተዋል።

ለዚህ  የተዳረገችውም ወደ ኩዌት የወሰዳት ስፖንሰሯ ወደ አገሯ ይመልሳት ዘንድ ያቀረበችለትን ጥያቄ ሳይቀበላት በመቅረቱ እንደሆነ ተገልጿል።

በዚህም ሳቢያ ኢትዮጵያዊቷ እስከ መደባደብ ሳትደርስ እንዳልቀረች የጠቀሰው የኩዌት ፖሊስ፤ የተሟላ መግለጫ ለመስጠት የዶክተሮች ሪፖርት እየተጠበቀ መሆኑን  አስታውቋል።

በተለየ መልኩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኩዌት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን  በአሠሪዎቻቸውና በስፖንሰሮቻቸው የተለያዩ በደሎች እየተፈፀሙባቸው እንደሚገኙ በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide