ሆስኒ ሙባረክ በዕድሜ ልክ እሥራት እንዲቀጡ ተወሰነ

ግንቦት ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የ 84 ዓመቱ ሙባረክ  ለፍርድ ቤቱ በከፍተኛ የጤና ችግር ላይ እንደሆኑ በማመልከት አስተያዬት ይደረግላቸው ዘንድ ጠይቀው እንደነበር የግብጽ መንግስታዊ ቴሌቪዥን ዘግቧል።

ሆስኒ ሙባርክን ለዕድሜ ልክ እሥራት ያበቃቸው፤ ባለፈው ዓመት የተካሄደውንና እርሳቸውን ከመንበራቸው የፈነቀላቸውን የግብጽ አብዮት  ለማክሸፍ በማሰብ  ባስወሰዱት የሀይል እርምጃ በርካታ ተቃዋሚዎች በመገደላቸው ነው።

ሙባረክ፤በዓረቡ ዓለም አብዮት ከተወገዱት መካከል ፦ ለፍርድ የቀረቡ  የመጀመሪያው  መሪ  መሆናቸውን ቢቢሲ  አመልክቷል።

የቀድሞው የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ሀቢቢ አል አድሊ በበኩላቸው ልክ እንደ ሙባርክ የዕድሜ ልክ እስራት የታለፈባቸው ሲሆን፤አራት የደህንነት ባለሥልጣናት ግን በነፃ ተሰናብተዋል።

የደህንነት ባለሥልጣናቱ እንዲፈቱ መወሰኑ፤ በአንዳንድ ታዳሚዎች ዘንድ ረብሻና አምባጓሮ  የፈጠረ ቢሆንም፤አብዛኞቹ  ታዳሚዎች ግን    ችሎቱ ከተጠናቀቀ በሁዋላ   በፈገግታ ሰላምታ በመለዋወጥ  በፍርዱ መደሰታቸውን ሲገልፁ ታይተዋል።

ሙባርክ ከዚህም ባሻገር ከሁለት ልጆቻቸው ጋር ፈፅመውታል በተባለው ሙስና የተመሰረተባቸው ክስ በተናጠል መታየቱን ቀጥሏል።

የቀድሞው የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ቻርለስ ቴይለር  በተከሰሱባቸው በርካታ ወንጀሎች ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው  ዘ-ሄግ የሚገኘው ዓለማቀፉ ፍርድ ቤት በቅርቡ  በ 50 ዓመት እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide