(ኢሳት ዲሲ–ጥር 24/2010)
የሕወሃት አገዛዝ ከውጭ ባንኮች በከፍተኛ ወለድ በተለያዩ ድርጅቶች ስም የተበደረውን ገንዘብ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት መክፈል እንደተሳነው ተዘገበ።
ለኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ የደረሰ መረጃ እንዳመለከተው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ከተበደረው ገንዘብ ባለፈው ጥርና የካቲት ከ2 ቢሊየን ብር በላይ በውጭ ምንዛሪ መመለስ ቢኖርበትም ክፍያውን ብሔራዊ ባንክ ሊፈጽም አልቻለም።
በጉዳዩ ላይ የገንዘብ ሚኒስቴር ምላሽ እንዲሰጥበት ቢጠይቅም ብሄራዊ ባንክን ጠይቁ ብሎ ጉዳዩን ችላ ማለቱንም ለማወቅ ተችሏል።
በኢትዮጵያ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ስራ ማስኬጂያና ለመሰረተ ልማቶች በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር ከተለያዩ ባንኮች በብድር መልክ በአገዛዙ ይወሰዳል።
ይህም ብድር በከፍተኛ ወለድ በጊዜ ገደብ የሚከፈል ነው።
ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን በኦ ኤም ኤን በኩል የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው ግን ለአባይ ግድብ፣ ለግቤ 3ና ለተለያዩ ፕሮጀክቶች የተሰጠ ብድርን በውጭ ምንዛሪ ችግር ምክንያት መክፈል አልተቻለም።
የኮርፖሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ ለገንዘብ ሚኒስቴር በጻፉት ደብዳቤ መሰረት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ባለፈው ጥርና የካቲት መከፈል የነበረበት 60 ሚሊየን ዶላር እና 83 ሚሊየን ዩሮ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት አልተከፈለም።
የዚህም ምክንያቱ ብሄራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪውን ለመፍቀድ ባለመቻሉ ነው ብለዋል።
ደብዳቤው የተጻፈላቸው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም ተከስተ ጣልቃ ከመግባት ይልቅ ችግሩን ለብሔራዊ ባንክ መልሰው መግፋታቸው ነው የተነገረው።
የብድሩ አለመከፈል በሀገሪቱ እዳ አመላለስ ላይ የራሱ የሆነ ተጽእኖ ሲኖረው ቀሪውን የብድር ገንዘብ ለማስለቀቅም ችግር እንደሚኖረው ተገልጿል።
ጉዳዩን በግልባጭ እንዲያውቁት የተደረገው የኮርፖሬሽኑ የቦርድ ሰብሳቢና የግድቡ አስተባባሪ ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል የሰጡት ምላሽም “እርሱት ምንም ችግር አያመጣም” የሚል እንደሆነም ተገልጿል።
ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ብድሩን የሰጡት የውጭ ባንኮች የቻይናው ኤግዚም ባንክ፣ ሲ ኢ ቲ ሰፕላይርስ ክሬዲት፣ ስታንዳርድ ባንክና ቨርጅኔት የተባሉ የፋይናንስ ተቋማት መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።
የኢሳት መረጃ ምንጮች የኢትዮጵያው አገዛዝ በውጭ ሀገር ላሉት ኤምባሲዎቹ የሚከፍለው የውጭ ምንዛሪ አጥቶ ዶላር በኢንቨስትመንትና በቦታ መስጠት ስም ከዲያስፖራው እንዲሰበስቡ ትዕዛዝ ማስተላለፉን መዘገባችን ይታወሳል።