(ኢሳት ዜና–ታህሳስ 4/2010)
የህግ የበላይነት ማስከበር ያለበት ሃይል የኦሮሞ ህዝብን መግደሉ ተቀባይነት እንደሌለውና ለህግ እንደሚቀርብ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ገለጹ።
ጉዳቱን ያደረሰው ሃይል ማን እንደጠራውና በማን ትዕዛዝ ቦታው ላይ እንደተገኘ አላወቅንም ብለዋል።
ሰሞኑን በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ሜታ ወረዳ ጨለንቆ ከተማ በሕወሃት የጦር አዛዦች የሚመራው ወታደራዊ ሃይል 18 ሰዎችን መግደሉንና በርካቶችን ማቁሰሉ ተዘግቧል።
ይህንን ግድያ ተከትሎ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ለማ መገርሳ በሰጡት መግለጫ በሜታ ወረዳ ጨለንቆ ከተማ 15 ሰዎች ተገድለዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎችም የመቁሰል አደጋ ደረሶባቸዋል ብለዋል።
ይህን ያህል አደጋ መድረሱ ክልላዊ መንግስቱን እንዳሳዘነ ተናግረዋል።
የህግ የበላይነትን ማስከበር ያለበት አካል የዚህ አይነት ድርጊት መፈጸሙ ተቀባይነት የለውም ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ድርጊቱን እንደሚያወግዘውም አስታውቀዋል።
እንደዚህ አይነት ድርጊት መፈጸሙንም እንቃወማለን፣ተቀባይነትም የለውም ብለዋል።
ይህን ድርጊት የፈጸመው ሃይል ማን እንደጠራው፣በማን ትዕዛዝ ቦታው ላይ ተገኝቶ በሕዝብ ላይ ጉዳት እንዳደረሰ የምናውቀው ነገር የለም ብለዋል።
ጉዳቱን ያደረሱትና እጃቸው ያለበት ሃይሎችን አጣርተን ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ ለህግ እንዲቀርቡ እንሰራለን ብለዋል።
በአቶ ለማ መገርሳ መግለጫ ላይ ለኢሳት አስተያየታቸውን የሰጡ የህግ ሙያተኞች ፕሬዝዳንቱ ያልጠራንው ሃይል ጉዳት አድርሶብናል ማለታቸው ህወሃቶች የራሳቸውን ህገመንግስት እንደጣሱ በግልጽ ያመላከቱበት ነው ብለዋል።
በኢህአዴግ ህገ መንግስት አንቀጽ 51 ንዑስ አንቀጽ 14 ላይ “ከክልል አቅም በላይ የሆነ የጸጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም በክልሉ መስተዳድር ጥያቄ መሰረት የሀገሪቱን የመከላከያ ሃይል ያሰማራል”እንደሚል ሙያተኞቹ አስታውሰዋል።
ሆኖም ፕሬዝዳንቱ በመግለጫቸው ላይ የተፈጠረው ችግር ከአቅማቸው በላይ እንዳልሆነና ለማንም ሃይል ጥሪ አለማቅረባቸውን መግለጻቸው በቀጥታ ህገ መንግስቱ መጣሱን ለማመላከት እንደሆነ ሙያተኞቹ አስረድተዋል።