የህወሃት አገዛዝ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ዘጋ

(ኢሳት ዜና–ታህሳስ 4/2010)

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተነሳውን ህዝባዊ አመጽ ተከትሎ የህወሃት አገዛዝ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን መዝጋቱ ታወቀ።

ፌስቡክና ትዊተርን የመሳሰሉት ማህበራዊ ድረ ገጾች ዝግ መሆናቸው ታውቋል።

ወትሮም ደካማ የነበረው የኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት አሁን ላይ ጭራሹኑ የፌስ ቡክና ትዊተር ድረገጾች እንዲዘጉ ሲደረግ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ የወጡ መረጃዎች እንዳይሰራጩ ለማድረግ መሆኑ ታውቋል።

በአዲግራት ዩኒቨርስቲ ዜጎች መገደላቸው በተለይ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች ተቃውሞ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ግቢውንም ለቀው እስከመውጣት ደርሰዋል።

የተማሪዎቹ ተቃውሞ ደግሞ ወደ ህብረተሰቡ ዘልቋል።

የሚካሄዱትን ተቃውሞዎች ተከትሎ የሚወጡት መረጃዎች የሚሰራጩት በፌስቡክ በቲዊተር በመሳሰሉት ማህበራዊ መገናኛ ብዙሀን በመሆናቸው ይታወቃል።

የመከላከያ ሰራዊት በተማሪዎች ላይ የሚፈጽመውን ግድያ፣ ድብደባ፣ እስር እና እንግልት እያጋለጡ የሚገኙ ማህበራዊ ሚዲያዎች መሆናቸው ደግሞ ለህወሃት አገዛዝ የሚመች አልሆነም።

ታዲያ የህወሃት አገዛዝ ይህንን ለማፈን የኢንተርኔት አገልግሎቱን ደካማ ከማድረጉ በተጨማሪ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን እንዲዘጉ አድርጓል።

ህወሀት የሚመራው መንግስት የኢንተርኔት አገልግሎትን ሲያቋርጥ እና ደካማ ሲያደርግ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

በሰኔ 2009 የብሔራዊ ፈተና በሚሰጥበት ወቅት ዘግቶት እንደነበር የሚታወስ ነው።

አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት የኢንተርኔት አገልግሎት ወትሮም እዚህ ግባ የማይባል ደካማ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ በአጠቃላይ እንዲዘጋ መደረጉ ስርአቱ በህዝብ ላይ እየፈጸማቸው ያሉትን ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች እንዳይጋለጡ ለማድረግ ነው።

ይህንኑ የማህበራዊ ድረ ገጾች አገልግሎት መቋረጥን ዋሽንግተን ፖስት፣ ፎክስ ኒውስና አሶሼትድ ፕሬስን የመሳሰሉ መገናኛ ብዙሃን በዘገባቸው አስፍረውታል።