በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የተጀመረው ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው

(ኢሳት ዜና–ታህሳስ 3/2010)

በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የተጀመረው ተቃውሞ መቀጠሉ ታወቀ።
በወልዲያ፣ በጎንደር፣ በባህርዳርና በደብረታቦር ዩኒቨርስቲዎች የተማሪዎች ተቃውሞ በመካሄድ ላይ ነው፡፡
የአጋዚ ሰራዊት በዩኒቨርስቲዎቹ ግቢ በመግባት ተማሪዎችን በመደብደብ ላይ መሆኑንም የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሻምቡ ግቢ ሁለት ተማሪዎች ተገድለዋል።


በአምቦ ዩኒቨርስቲ ተማሪው የአቋም መግለጫ በማውጣት ትምህርት ማቆሙን አስታውቋል።
የህወሃት አገዛዝ ደጋፊ የሆኑ አክቲቪስቶች መንግስት ዩኒቨርስቲዎችን እንዲዘጋ ግፊት እያደረጉ መሆኑም ተሰምቷል።
በአጠቃላይ በሀገሪቱ 13 ዩኒቨርስቲዎች የመማር ማስተማር ሂደቱ ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል።
በወልዲያ ዩኒቨርስቲ የተነሳው ተቃውሞ በቀጠለበት በዛሬው ዕለት ተማሪዎች በአጋዚ ሃይል መደብደባቸው እየተነገረ ነው።
ትላንት ምሽት መውጫና መግቢያ የተከለከሉ ተማሪዎች የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ ነው።
ሴት ተማሪዎች በማደሪያቸው ታግተዋል።ወንዶቹ ከአጋዚ ጋር ተፋጠዋል።
በጎንደር ዩኒቨርስቲ ትላንት የህወሃት አገዛዝ ከስልጣን እንዲወርድ የተጠየቀበትን የተማሪዎች ተቃውሞ ተከትሎ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአጋዚ ጦር ዛሬ ወደ ግቢው ዘልቆ ገብቷል።
በተማሪዎች ላይ ድብደባ በመፈጸም ላይ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ከባድ ጉዳት መድረሱም ታውቋል።
በደብረታቦር ዩኒቨርስቲ ትላንት የተነሳው ተቃውሞ ቀጥሎ ዛሬም በአጋዚ ጦርና በተማሪዎች መካከል ግጭት መፈጠሩ ተገልጿል።
በርካታ ተማሪዎች መደብደባቸውንና የታሰሩም እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል።
አንድ የደብረታቦር ዩኒቨርስቲ ተማሪ ከዩኒቨርስቲው ግቢ ውስጥ እንዳይወጡ መታገዳቸውን ለኢሳት ገልጿል።
በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ በተለይም በዘንዘልማ ካምፓስ ታምቆ የነበረው የተማሪዎች ቁጣ ዛሬ ወደ ተቃውሞ መቀየሩ ተሰምቷል።
ዙሪያውን ከቦ ሲጠባበቅ የነበረው የአጋዚ ሰራዊት ከምሽት ጀምሮ ወደ ግቢው መግባቱ የተገለጸ ሲሆን ከተማሪዎች ጋር ግጭት መፈጠሩም ታውቋል።የተጎዱ ተማሪዎች ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።
ተቃውሞው በፔዳ ካምፓስም እንደሚጀምር ይነገራል።
የወለጋ ዩኒቨርስቲ ዛሬ በተነሳው ግጭት ሁለት ተማሪዎች መገደላቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በሻምቡ ካምፓስ የተፈጠረውን ግጭት በተመለከተ የሁለት ተማሪዎች ግድያ እንደተመዘገበም የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ አረጋግጠዋል።
በአምቦ ዩኒቨርስቲ ዛሬ በተማሪዎችና በአጋዚ ጦር መካከል የነበረው ፍጥጫ ወደ ግጭት ተቀይሮ በርካታ ተማሪዎች መደብደባቸውን ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
ተማሪዎቹ የአቋም መግለጫ አውጥተው ትምህርት አቁመዋል።